በአፋር አሳይታ አካባቢ መንገዶች ተዘግተው መዋላቸው ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 7/2011)በአፋር በነዋሪዎችና በመከላከያ ሰራዊት መካከል በተፈጠረ ግጭት የአሳይታ አካባቢ መንገዶች ተዘግተው መዋላቸው ተገለጸ።

ግጭቱ የተፈጠረው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱ ችግሮች ባልተፈቱበት ሁኔታ የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ አባላት ለሌላ ዓላማ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን  ተከትሎ ነው።

የኢሳት ምንጮች ባደረሱን መረጃ ላይ እንደተመለከተው የመከላከያ ሰራዊቱ ከኮንትሮባንድ ንግድ ጋር የተያያዘ ዘመቻ ተሰጥቶት በመጓዝ ላይ እያለ ከህዝብ ተቃውሞ ገጥሞታል።

በአፋር የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግስቱ የህዝብን ጥያቄ መመለስ አልቻሉም በሚል የተነሳው ተቃውሞ በተለያዩ አከባቢዎች እንደቀጠለ መሆኑ ታውቋል።

በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የተነሳው ተቃውሞ በየጊዜው በህዝቡ ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ታጣቂ ሃይሎችን ለህግ ሳያቀርብ ወዴትም አይሄድም በሚል ነው ብሏል የአፋር ህዝብ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ አካድር ኢብራሒም።

እንደ አካድር አባባል የአፋር ሕዝብ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ እምነት ማጣቱ ሌላኛው ችግር ነው ብሏል።

በየቀኑ ሕይወቱን እያጣ ላለው የአፋር ህዝብ የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግስቱ በአስቸኳይ መፍትሄ ሊያመጡ ይገባል ብሏል።

በዚህ ወቅት ጉዳት እየደረሰበት ስላለው የአፋር ህዝብ መንግስት ብቻ ሳይሆን መገናኛ ብዙሃንም ትኩረት ነፍገውታል ሲል ቅሬታውን አቅርቧል።