በአጋሮ ከተማ በተነሳ ተቃውሞ የአንድ ሰው ህይወት አለፈ

በአጋሮ ከተማ በተነሳ ተቃውሞ የአንድ ሰው ህይወት አለፈ
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 02 ቀን 2011 ዓ/ም ) ዛሬ አርብ የከተማው ከንቲባ አቶ ናዚሙ ሁሴን፣ የጎማ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ራይስ እንዲሁም የድርጅት ቢሮ ሃላፊው አቶ ነዚህ ሙሃመድ አሚን እንዲወርዱ ለመጠየቅ በተሰባሰቡ ነዋሪዎች ላይ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በወሰዱት እርምጃ በሞተስ ሳይክል ሲጓዝ የነበረ አንድ ሰው በጥይት ተመትቶ ህይወቱ አልፏል።
በከተማዋ የንግድ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተዘግተው ውለዋል።
ተቃውሞው ካለፈው ማክሰኞ የጀመረ ሲሆን፣ ለዛሬ መልስ እንደሚሰጥ ቀጥሮ ተይዞ ነበር። ትናንት ምሽት ወጣቶች በዛሬው እለት ተቃውሞ እንደሚኖር ሲቀስቀሱ ያመሹ ሲሆን፣ የከተማው መስተዳድርም ምንም አይነት የተቃውሞ ሰልፍ እንዳልተፈቀደ በመግለጽ፣ ነዋሪዎች ወደ አደባባይ እንዳይወጡ ፣ በሚወጡት ላይ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ ሲያስጠነቅቅ ነበር። ዛሬ ወጣቶቹ አደባባዩ አካባቢ መሰባሰብ ሲጀምሩ ወደ ከተማዋ የገቡት ወታደሮች ተኩስ በመክፈት ወጣቶችን ሲበትኑ የአንድ ሰው ህይወት አልፏል።
በጉዳዩ ዙሪያ የከተማውን ከንቲባ ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።