በአዲስ አበባ ዛሬም ግጭት ተቀስቅሶ ዋለ

በአዲስ አበባ ዛሬም ግጭት ተቀስቅሶ ዋለ
( ኢሳት ዜና መስከረም 04 ቀን 2011 ዓ/ም ) በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራውን ኦነግ ለመቀበል የሚደረገውን ዝግጅት ተከትሎ የተነሳው ውጥረት እያየለ በመሄዱ ዛሬ በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት ተፈጥሯል። በርካታ ቄሮዎች ወደ መሃል አዲስ አበባ በመግባት የተለያዩ መፈክሮችን ሲያሰሙ የዋሉ ሲሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በቄሮዎችና በአዲስ አበባ ወጣቶች መካከል በነበረው ድንጋይ ውርወራና ፖሊስ ግጭቱን ለማስቆም በመወሰደው እርምጃ የተወሰኑ ሰዎች ተጎድተዋል።
የሰብአዊ መብት ታጋዩ ዮናታን ረገሳ በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች ሰላም መሆኑን፣ ወደ አስኮና ፒያሳ አካባቢ ግጭት መቀስቀሱን ገልጾ፣ በአሁኑ ሰዓት ወጣቱ በተለያዩ ወሬዎች ስሜታዊ እየሆነ ነው ብሎአል።
በሌላ በኩል “ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፊት አውራሪነት ተግባራዊ በመሆን ላይ ያለው አገራዊ ለውጥ ከባንዲራ ቀለማት በላይ ትላልቅ ዓላማዎችን አንግቦ የተነሳ ነው። የለውጡ ዓላማ እውነተኛ ፍትህን፣ እኩልነትን፣ ነጻነትንና ልማትን ማረጋገጥ ነው። ጉዳዩ ይህ ሆኖ ሳለ ገና ከወዲሁ በጥቃቅን ልዩነቶች ላይ ተመስርቶ የሚካሄድ አፍራሽ እንቅስቃሴ በምንም መልኩ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።” ሲል የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
“በባንዲራ ቀለምም ይሁን ከፖለቲካ ድርጅቶች አርማዎች በላይ ባሉ በርካታ ጉዳዮች ላይ ያሉ የአመለካከት እና የሃሳብ ልዩነቶች ሁሉ እንደ ፀጋ እና እንደበረከት ሊቆጠሩ እንደሚገባ” የገለጸው መንግስት “ ይህንን ዕውነታ ተቀብሎ ልዩነቶችን በሰለጠነ አካሄድ፣ በውይይት እና በሃሳብ ትግል ብቻ መፍታትን ከዚህ በኋላ ባህላችን ልናደርግ ይገባል።” ብሎአል።