በአዲስ አበባ ከ2500 በላይ የሚሆኑ ቤቶችን የማፍረስ ዘመቻ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ከ2500 በላይ የሚሆኑ ቤቶችን የማፍረስ ዘመቻ ተጀመረ
(ኢሳት ዜና የካቲት 30 ቀን 2010 ዓ/ም) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ስሙ ኪዳነ ምህረት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቤት ሰርተው ይኖሩ የነበሩ ከ2500 በላይ አባዎራዎችና እማዎራዎች፣ ቤታቸው በላያቸው ላይ እንዲፈርስባቸው ተደርጓል። ፈረሳውን ተከትሎ በአማካኝ ከ12 ሺ ያላነሱ ሰዎች ቤት አልባ ይሆናሉ።
በመላው አገሪቱ ከቤት ፈረሳ ጋር በተያያዘ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ገንዘባቸውን አፍስሰው ግንባታ ከፈጸሙ በሁዋላ፣ ህገ ወጥ ግንባታ በሚል ምክንያት ቤት እና ንብረት አልባ ሆነዋል። ይህንን እርምጃ የተቃወሙ ዜጎች ለሞት፣ለእስርና ለድብደባ ተዳርገዋል። በመጀመሪያ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች መፍረሳቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የአሁኑ እርምጃም ሁለተኛውን አዋጅ ተገን በማድረግ የተወሰደ ነው።