በአዲስ አበባ ከ2ሺህ በላይ ነዋሪዎች ቤተክርስቲያን መጠለላቸው ታወቀ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 4/2011) ከአዲስ አበባ በተለምዶ አጃምባ በሚባል አካባቢ ቤት ሰርተው ለዓመታት የቆዩ ከ2ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ቤተክርስቲያን መጠለላቸውን ገለጹ።

ህገወጥ ናችሁ ተብለው በሌሊትበተኙበት በአፍራሽ ግብረሃይል ቤታቸው የፈረሰባቸው ተፈናቃዮች በፋኑዔል ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ተጠልለው መኖር ከጀመሩ 15ቀናትያለፋቸው መሆኑን ለኢሳት ገልጸዋል።

በወቅቱ በድንገት በተወሰደው የማፍረስ ተግባር በተፈጠረ ግርግር በጥይትና በግፊያ 3 ሰዎች መሞታቸው ተመልክቷል።

የከተማው አስተዳደር ምላሽ አልሰጠንም የሚሉት ተፈናቃዮቹ ህጻናትን ጨምሮ ዜጎች በረሃብ እየተሰቃየን ነው ብለዋል።

ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት ከ8 እስከ 15 ዓመታት ድረስ ከኖሩበት አካባቢ እንዲለቁ ተሰጥቶአቸው የነበረው የጊዜ ገደብ 7 ቀናት ብቻ ነበር።

በእነዚያ ቀናት ተፈናቃዮቹ ህጋዊነቱን ያሳያል ያሉትን የተለያዩ ማስረጃዎችና ሰነዶችን በመያዝ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ለማቅረብ ቢመላለሱም ምላሽ የሚሰጣቸው እንዳጡ ነው ለኢሳት የገለጹት።

በድንገት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በፌደራል ፖሊስ የታጀበ አፍራሽ ግብረሃይል አካባቢውን በመውረር ቤት ማፍረስ መጀመሩን የሚገልጹት ተፈናቃዮቹ፣ በተኛንበት በላያችን ላይ ዶዘር ተላከብን ሲሉ የደረሰባቸውን በምሬት ይናገራሉ።

በዚያ ለሊት 405 መኖሪያ ቤቶች ወደ ፍርስራሽነት ተለውጠዋል።

በውስጡ የነበሩ የቤት እቃዎች መትረፍ አልቻሉም። የቻልነውን ለማዳን ሞክረናል የሚሉት ተፈናቃዮቹ መንግስት እንዲህ ዓይነት የጭካኔ ተግባር በገዛ ዜጎቹ ላይ መውሰዱ አሳዝኖናል ሲሉ ገልጸዋል።

በወቅቱ በተፈጠረ ግርግር ሶስት ሰዎች ሞተውብናል፣ በጥይትና በትርምሱ ምክንያት የተገደሉብንን በወጉ እንኳን መቅበር አልቻልንም ብለዋል።

መሄጃ መጠጊያ አጥተው የተንከራተቱት ተፈናቃዮች በአቅራቢያቸው በሚገኘው የፋኑዔል ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ለጊዜው ተጠግተው በመኖር ላይ ናቸው።

ላለፉት 15 ቀናት የአካባቢው ነዋሪ የሚችለውን እያደረገልን ቆይተናል።

አሁን ግን ችግሩ እየባሰ በመምጣቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ይርዳን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ህጻናት እየተራቡብን ነው፣ እዚህም የሞቱብን አሉ፣ ከ100 በላይ የሚሆኑት ተፈናቃዮች በብርድና በተለያዩ በሽታዎች ምክንያት ሆስፒታል ገብተዋል የሚሉት ተፈናቃዮች አፋጣኝ ድጋፍ ካልተደረገልን የከፋ ቀውስ ውስጥ እንገባለን ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በፋኑዔል ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ድንኳን ጥለው የሚኖሩት ተፈናቃዮች ከመንግስትም ሆነ ከቀይመስቀል የተሰጣቸው ድጋፍ የለም።

ነፍሰጡሮችና ለመውለድ የደረሱ እናቶች በድንኳን ውስጥ በስቃይ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ህጻናት ከፍተኛ ጉዳት ላይ ናቸው ድረሱልን ነው የሚሉት ተፈናቃዮቹ።

ለጊዜው ባይሳካልንም ጉዳዩን ይዘን ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ምላሽ ለማግኘት ጥረት እያደረግን ነው።