በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የ28 ሰዎች ተገድለዋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 14/2011) በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ከተፈጠረው ሁከት ጋር ተያይዞ የ28 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ።

መስከረም 7/2011 በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተገደሉትን 5 ሰዎች ጨምሮ ከመስከረም 2 እስከ መስከረም 7/2011 28 ሰዎች መገደላቸውን የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽነር ናቸው።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሜጀር ጄኔራል ደግፌ በዲ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከግድያውና ሁከቱ ጋር በተያያዘ በሺዎች የሚቆጠሩ የተያዙ ቢሆንም እየተጣራ በከፊል መለቀቃቸውን ገልጸዋል።

ከነዚህ ውስጥ 1 ሺ 200 የሚሆኑት ተለይተው ወደ ጦላይ መወሰዳቸውንም ገልጸዋል።

እነዚህም ተሃድሶ ከተሰጣቸው በኋላ ይለቀቃሉ ብለዋል።

ሆኖም 174 ሰዎች ለፍርድ እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል።

እነዚህ 174 ሰዎች በአዲስ አበባ ከሚገኙት አስሩም ክፍለ ከተሞች የተያዙ መሆናቸውም ተመልክቷል።

ከመስከረም 2 እስከ 7 በከተማዋ ውስጥ በነበረው ግርግር በባንክ ላይ የዘረፋ ሙከራ እንደነበር፣በተሽከርካሪዎችና በሱቆች ላይ ጥቃት መሰንዘሩንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

ፖሊስ በቁማርና በሺሻ ቤቶች ላይ በወሰደው ድንገተኛ ርምጃ ከ1 ሺ 500 ሰዎች በላይ መታሰራቸውን የፖሊስ ኮሚሽነሩ ሜጀር ጄኔራል ደግፌ በዲ ተናግረዋል።

ከነዚህ ውስጥ 1 ሺ 459ኙ ከሺሻ ቤቶች ውስጥ የተያዙ መሆናቸውም ተመልክቷል።

በሺሻ ቤቶቹ ውስጥ ከተያዙት መካከል የውጭ ሃገር ፓስፖርት የያዙ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሃገር ዜጎች እንደሚገኙበትም ተመልክቷል።

የሺሻና የቁማር ቤቶቹን የከፈቱትን ሰዎች ግን ፖሊስ ማግኘት አለመቻሉን የፖሊስ ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ደረጃ የተደራጀ ዘረፋ በመካሄድ ላይ መሆኑንም የፖሊስ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ይህ በመሳሪያ ጭምር ተደግፎ የሚካሄደውን ዘረፋ ከአዲስ አበባ ውጪ የመጡ ግለሰቦች እንደሚሳተፉበትም ነው ኮሚሽነሩ የጠቆሙት።

በተለይ ከደሴ፣ጎንደርና አርባምንጭ የመጡ የተደራጁ ዘራፊዎች በቀን ብርሃን ከግለሰብ ላይ ተሽከርካሪ ነጥቆ እስከመውሰድ የተደራጀ የዘረፋ ተግባር መፈጸማቸውን ኮሚሽነሩ ሜጀር ጄኔራል ደግፌ በዲ ገልጸዋል።