በአዲስ አበባ ባላደራው ምክር ቤት (ባልደራስ) አባላት ላይ የሚደርሰው እንግልትና እስር ቀጥሏል

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 16/2011)በአዲስ አበባ ባላደራው ምክር ቤት (ባልደራስ) አባላት ላይ እየደረሰ ያለው እንግልትና እስር መቀጠሉ ተገለጸ።

የምክር ቤቱ አባል አቶ ሽመልስ ለገሰ ዛሬ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ጉዳይ ሊከታተሉ በሄዱበት በፖሊስ መታሰራቸው ተሰምቷል።

ከሰአታት ክርክር በኋላም አቃቤ ህግ ስህተት አላገኘሁባቸውም ስለዚህ ክስ አልመሰርትም በማለቱ መለቀቃቸው ነው የታወቀው።

በአዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ ቤታቸው ፈርሶ ቤት ሳያገኙ በላስቲክ ያሉ ዜጎችን ጉዳይ ሊያዩ የባለደራ ምክር ቤቱ አባል አቶ ሽመልስ ለገሰ ወደ ስፍራው ይሄዳሉ።

በአካባቢውም ደርሰው ቤት ከፈረሰባቸው ዜጎች የተነሳውን ቅሬታ ለማጣራት ወደ ሚመለከተው አካል መንገድ ቢጀመሩም ደንብ እናስከብራለን የሚሉት አካላት ግን ማረፊያቸውን በፖሊስ ጣቢያ እንዳደረጉት ይናገራሉ አቶ ሽመልስ።

አቶ ሽመልስ እንደሚሉት በፖሊስ ጣቢያ የነበራቸው ቆይታ የሳቸውን ጉዳይ በሚመለከት የተወራበት ሳይሆን ከኮማንደሩ የተሰጣቸው አላግባብ ንግግር ያዳመጡበትና የአቃቤ ህጎችን ትክክለኛ ውሳኔ የታዘቡበት ነው።

ያገኟቸው ኮማንደር ችግርን ከመፍታት ይልቅ ቁልፌን ውሰዱና እናንተ ስሩ፣በእናንተ ምክንያት ስራ መስራት አልቻልንም በሚል ማመናጨቅና አላግባብ ንግግሮችን ሲናገሩ እንደነበርም ገልጸዋል።

አቶ ሽመልስ እንደዚህ አይነት ማፈናቀሎች ሲፈጸሙና ዜጎች ስለመብታቸው ሲከራከሩ ያለውን ሁኔታ ማንም እንዲያይ አይፈቀድም ይላሉ።–በአካባቢው ምስል የሚቀርጽም ሆነ ድምጽ የሚቀርጽ ካለ እንደሚነጠቅ በመጠቆም።

ያለው ሁኔታ ሁሉ እንደቀድሞው አላግባብ ዜጎችን የማንገላታትና የማሰቃየት ጉዳይ ነው ብለዋል።

ባለ አደራ ምክር ቤቱ እነዚህ ጉዳዮች ለመከታተልና የዜጎችን ድምጽ ለማሰማት ቢሮውን ከፍቶ እየሰራ ባለበት በዚህ ወቅት እየደረሰበት ያለው እንግልትና ወከባ ቀጥሏል ይላሉ አቶ ሽመለስ።

ነገር ግን ምክር ቤቱ የሚደርስበትን እንግልት ሁሉ ተቋቁሞ ለዜጎች መብት መከራከሩን ይቀጥላል ብለዋል።

በቅርቡ በአዲስ አበባ ክረምትን ጠብቆ ይፈርሳሉ ስለተባሉት ቤቶች ጉዳይም ባላደራ ምክር ቤቱ ባልደራስ ዝም አይልም ያላሉ አቶ ሽመልስ።