በአዲስ አበባ ሶስት የፌደራል ፖሊሶች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 24/2011)አዲስ አበባ ላይ ሶስት የፌደራል ፖሊስ አባላት መገደላቸው ተገለጸ።

5 ፖሊሶችም መቁሰላቸው ታውቋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩም የፖሊሶቹን መገደል አረጋግጠዋል።

አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወሎ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ትላንት ሌሊት ላይ የተፈጸመውና ለፖሊሶቹ መገደል ምክንያት የሆነው ነገር የተፈጠረው በመጠጥ ሃይል የተገፋፋው የፖሊስ አባል ሁለት ባልደረቦቹን በመግደሉ እንደሆነ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

ሌሎች ፖሊሶች ደግሞ አደጋውን እያደረሰ ያለውን ፖሊስ ለማስቆም በከፈቱት ተኩስ ጥቃቱን ያደረሰው ፖሊስ ሕይወት ማለፉ ታውቋል።

ሟቹ ፖሊስ አስቀድሞ በከፈተው ተኩስ ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላትን መግደሉ ነው የተሰማው።

ተጨማሪ አምስት ፖሊሶችም ቆስለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚኖሩበትን ሕንጻ በሚጠብቁ ፖሊሶች መካከል የተፈጠረውን ግጭት በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ከመጠጥ ሃይል ጋር የተያያዘ እንደሆነ ቢገልጹም የአካባቢው ሃላፊ ኮማንደር ብርሃነ ቢሆን ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ በፖሊሶች መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ወደ መሳሪያ መማዘዝ ማምራቱን ገልጸዋል።

ከግድያው ጋር በተያያዘ የቦሌ መንገድ እስከ ጠዋቱ 3 ሰአት ዝግ ሆኖ መቆየቱም ተመልክቷል።