በአዲስ አበባ ስለተፈጸመው የጅምላ እስራት በቂ ማብራሪያ ይሰጥ ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 18/2011) በአዲስ አበባ ለተፈጸመው የጅምላ እስራት መንግስት በቂ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠየቀ።

የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ሰመጉ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የጅምላ እስራቱን በተመለከተ በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ።

ህገ መንግስታዊ መብትን በጣሰ መልኩ የተፈጸመው የጅምላ እስር ግልጽነት የጎደለው የፖሊስንም ርምጃ ህጋዊነቱን ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ሲል ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በመግለጫው ገልጿል።

ክስ ሳይመሰረትባቸው የታሰሩ ዜጎች በአስቸኳይ እንዲፈቱም ጉባኤው በመግለጫው ጠይቋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ በመዲናዋ በተካሔደው የጅምላ እስር በአጠቃላይ ወደ ሶስት ሺህ የሚደርሱ ዜጐችን ማሰሩን አስታውቀዋል።

የጅምላ አፈሳው በከተማዋ በነበረው (ሁከት) ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርገዋል የተባሉ 1,204 ዜጎችን ጨምሮ፤ በጫት ቤት፣ በሺሻ ቤትና በቁማር ቤት በተገኙ ወጣቶች ላይ መሆኑንም አመልክተዋል’።

ይህን የጅምላ አፈሳ አስመልክቶ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ሰመጉ መግለጫውን አውጥቷል።

ሰመጉ በመግለጫው ምንም እንኳን ፖሊስ ከተማዋን ለማረጋጋት ርምጃ መውሰዱ ተገቢ ቢሆንም ከሕግ አግባብ ውጪ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መጠነ ሰፊ እስር መፈፀሙ አግባብነት የለውም ብሏል።

የጅምላ እስራቱ ሠላማዊ ዜጐችንም ጭምር ዒላማ ማድረጉ፣ ጥቂት የማይባሉ ታሳሪዎች ላይ ፖሊስ ድብደባ መፈፀሙ፣ ብሎም ዘላቂ የአካል ጉዳት ማድረሱ፣ በሕግ ወንጀል እንደሆነ በግልፅ ባልተደነገጉ ሥፍራዎች ያገኛቸውን ዜጐች ማሠሩ፣ ከሕግ አግባብ ውጪ ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ እስራቶቹ መፈፀማቸው ጉዳዩን ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል ብሏል መግለጫው።

እንደ መግለጫው ከሆነ ሠላማዊውን ሕዝብ ጭንቀት ውስጥ በከተተና ግልፀኝነት በጐደለው መልኩ የጅምላ እስሩ መካሄዱ ብሎም መነሻ ምክንያት እና ታሳሪዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ለሕዝብ ይፋ አለማድረጉ የፖሊስን ርምጃ ሕጋዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነው።

ሰመጉ ያነጋገራቸውና በጅምላ ከታሰሩት ዜጎች መካከል ፖሊስ በምርመራ ወቅት የተቀናቃኝ ፓርቲዎች አመራሮች ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ የአቀባበል ዝግጅቱን ለምን አስተባበራችሁ፣ ለምን የፓርቲዎቹ ደጋፊ ሆናችሁ የሚሉና ተመሳሳይ የምርመራ ጥያቄዎች እንደቀረቡላቸው ለሰመጉ አስረድተዋል፡፡

ከቡራዩ ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረግ ሲያስተባብሩ የነበሩ የአዲስ አበባ ወጣቶች በብዛት መታሠራቸውን ሰመጉ መመልከቱን በመግለጫ አስፍሯል።

ይህን አስመልክቶ  ፖሊስ የሰጠው “ሁከትን የማረጋጋት“ ምክንያት የፖሊስን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል ብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሁከቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ነበሩ ያላቸውን 1,204 ዜጐች ለተሃድሶ ስልጠና በሚል ምክንያት ወደ ጦላይ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፕ መውሰዱንም አረጋግጧል፡፡

ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የተያዙ ሰዎች በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለባቸው በግልፅ ቢደነግግም ፖሊስ ይህንን የታሳሪዎች ህገ-መንግስታዊ መብት በመጣስ ካለፍርድ እና ገደቡ ለማይታወቅ ግዜ ታሳሪዎችን ወደ ወታደራዊ ካምፕ ወሰዷል፡፡

ፖሊስ ታሳሪዎቹን በመደበኛ ፖሊስ ጣቢያዎች ለማቆየት ያልቻለበትንም ምክንያት ግልፅ አላደረገም ብሏል መግለጫው፡፡

ይህ የፖሊስ ድርጊት የዜጐችን ሕገ መንግስታዊ መብት በግልፅ የጣሰ በመሆኑ ከሕግ አግባብ ውጪ የተያዙ፣ ክስ ሳይቀርብባቸው ወይም ሳይፈረድባችው የታሰሩ ዜጐች በኣአስቸኳይ እንዲፈቱ ሰመጉ ጠይቋል፡፡

ሃገሪቱ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ውስጥ በነበረችበት ወቅት በተለያዩ ወታደራዊ ካምፖች ታስረው የነበሩ ዜጐች ይደርስባቸው የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ትውስታ ከአእምሮ ባልጠፋበት በዚህ ወቅት ለስልጠና በሚል ሠበብ መንግስት ዜጐችን ወደ ወታደራዊ ካምፕ ማጋዙ ለሌላ ዙር መጠነ-ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳያጋልጣቸው ሲል ሰመጉ ስጋቱን ገልጿል፡፡

በመሆኑም በሁከት እና በግርግር ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል በሕግ ጥላ ስር የሚገኙ ዜጐች የሰብዓዊ መብታችውን በጠበቀ መልኩ የመያዝ መብታችው እንዲከበር፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በወዳጆቻቸው እና በሕግ አማካሪዎቻቸው የመጐብኘት መብታቸው እንዲጠበቅላቸው፤ እንዲሁም ክስ ያልተመሠረተባቸው ዜጐች በፍጥነት እንዲለቀቁ ሰመጉ ጠይቋል፡፡

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሔደው ጅምላ እስር ከመንግስት በኩል ቢሆን ሙሉ ማብራሪያ ሊሰጥበት ይገባል ብሏል ሰመጉ በመግለጫው፡፡