በአወዳይ በርካታ ዜጎች ተገደሉ

የጎንደር ህዝብ ህዝባዊ ተቃውሞ በሚያደርግበት እለት ተመሳሳይ ተቃውሞ ያደረጉት የአወዳይ ከተማ ነዋሪዎች በአጋዚ ወታደሮችና በፌደራል ፖሊሶች ተጨፍጭፈዋል።

እስካሁን ባለው መረጃ 6 ሰዎች የተገደሉ መሆኑ ሲግለጽ፣ አንዳንድ ነዋሪዎች ግን የሟቾቹ ቁጥር በርካታ ነው ይላሉ። ከ20 በላይ ሰዎችም ቆስለዋል።

ከትናንት ጀምሮ መንገዶች ተዘጋግተው የዋሉ ሲሆን፣ ዛሬ አወዳይ ሙሉ በሙሉ ጭር ብላ መዋሉዋንና ከተማዋ ሙሉ በሙሉ በወታደሮች ቁጥጥር ስር መግባቷን የአይን እማኞች ገልጸዋል።

“ ጸሃይ አይጠልቅባትም የምትባለዋ አወዳይ፣ ጨለማ ውስጥ ገብታለች “ ሲሉ አንድ የከተማው ነዋሪ ከተማዋ አሁን ስላለችበት  ሁኔታ ተናግረዋል።

በሚቀጥለው ሳምንት በመላው ኦሮምያ የተቃውሞ ሰልፍ ይካሄዳል ተብሎም ይጠበቃል።