በአማሮ ወረዳ ከአመት በላይ የዘለቀው ግጭት እንደገና አገረሸ

በአማሮ ወረዳ ከአመት በላይ የዘለቀው ግጭት እንደገና አገረሸ
( ኢሳት ዜና መስከረም 04 ቀን 2011 ዓ/ም ) ከ 15 ወር በላይ ያስቆጠረዉና መፍትሄ ያጣዉ በደቡብ ክልል አማሮ ወረዳ በሚገኙ የኮሬ ብሔረሰብ እና ቡርጂ ወረዳ በሚገኙ ቡርጂ ብሔረሰብ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን በሚኖሩ ጉጂ ብሔረሰቦች መካከል የተነሳዉ ግጭት ሰሞኑንም ተባብሶ በመቀጠል በሰዉ ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል።
ከአማሮ ወረዳ ደርባ ቀበሌ ላይ ከ 70 በላይ ከብቶች መዘረፋቸውን ተከትሎ፣ በደርባ፣ ቲፋቴ፣ ዬሮ፣ ጉሙሬ እና አልፋጮ ቀበሊዎች ከፍተኛ የተኩስ ልዉዉጥ እየተደረገ እንዳለ እስከ አሁን ከአማሮ በኩል ባንዲሩ ባጄ የተባለ የ30 አመት አርሶ አደር ሲገደል፣ ሌላ ተሰሎንቄ ስፋደ የተባለ ወጣት ደግሞ በከፍትኛ ሁኔታ ቆስሎ በኬሌ ሆስፒታል እየተረዳ ነው።
በተመሳሳይ መልኩ በቡርጂ ወረዳም በሰሞኑ ጫነ ጫዶ የተባሉ አባትና መቻል ጫኔ የተባለው ልጃቸው በእርሻ ቦታቸዉ ላይ ጥቃት ተሰነዝሮባቸው፣ አባትየው ህይወታቸው ሲያልፍ፣ ልጃቸው በከፍተኛ ሁኔታ ቆስሏል። ይህን ተከትሎም በቡርጂ ወረዳ 7 ቀበሊያት ላይ ከፍተኛ የተኩስ ልዉዉጥ የተደረገ ሲሆን፣ ተኩሱ እስከዛሬ ቀጥሏል። መከላከያ ሰራዊት በሁለቱም ወረዳዎች ሰፍሮ የሚገኝ ቢሆንም መኖሪያቸዉ ከግጭቱ አካባቢ ራቅ ያለ በመሆኑ ግድያዎችን ማስቆም አልቻሉም
ከሁለቱም ወረዳዎች የተፈናቀሉ ከ 30 ሺ በላይ ዜጎች ጉዳይም ከጊዜ ጊዜ አሳሳቢነቱ እየጨመረ እንደመጣ ነዋሪዎች ይናገራሉ።