በአማራ ክልል የጸጥታ ችግር እየተባባሰ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 8/2011) በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ በመሻሻል ፈንታ እየተባባሰ በመምጣቱ የህዝቡ ደህንነት ለአደጋ መጋለጡን የክልሉ መንግስት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በወቅታዊ የክልሉ ጉዳይ ላይ የተሰጠው መግለጫ እንዳመለከተው በተለይም በምዕራብ እና ማዕከላዊ ጐንደር የበርካታ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ፣አካል ያጐደለና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐችን ንብረትና ቤት አልባ ያደረገ ችግር እየተፈፀመ ይገኛል፡፡

እናም ከዚህ በኋላ እንዲህ አይነት ችግሮችን እንደማይታገስ የክልሉ መንግስት አስታወቋል።

የአማራ ክልል መንግስት እንዳስታወቀው በክልሉ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው ጥቃት አካባቢው  እንዳይረጋጋ አላማ አድርገው በሚንቀሳቀሱና ከጀርባ ባሉ ሃይሎች አማካኝነት ነው።

በተለይም በቅማንት ስም የተደራጀው የጥፋት ሃይል እና በአማራ ስም እየማሉ እየተገዘቱ ሕዝቡን ለጥቃት የሚያጋልጡ የታጠቁ ሃይሎች የሚፈጽሙት ድርጊት እየተባባሰ መቷል ብሏል፡፡

እነዚህ በሁለት ጐራ ተሰልፈው ለጥፋት የተሰማሩ ሃይሎች በዋነኝነት ወንድማማቹን የቅማንት እና የአማራ ህዝብ የጥቃት አላማቸው በማድረግ ጥፋት እየፈፀሙ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

እናም በንፁሃን ዜጐች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በአስቸኳይ መቆም አለበት ነው ያለው የአማራ ክልል መንግስት ፡፡

በዚህም ምክንያት የክልሉ የፀጥታ ሃይል ሰው በመግደልና በማፈናቀል አመራር የሰጡና ያስተባበሩ ቡድኖችና ግለሰቦችን ይዞ ለህግ በማቅረብ ፣በአመፀኞች ላይ ተመጣጣኝ ርምጃ በመውሰድ ዜጐችን ከጥቃት እንዲከላከል መታዘዙን አስታወቋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የፌዴራል መንግስት የፀጥታ ሃይሎች በተለይም የመከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ህዝቡን ከነዚህ የታጠቁ ሃይሎች ጥቃት ለመከላከል በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የክልሉ የፀጥታ ሃይልና በየደረጃው ያለው የመንግስት መዋቅር በቅንጅት እንዲሰራም አሳስቧል።

ህዝቡን ለስጋት በሚዳርግ ሁኔታ በቡድን ተደራጅቶ ከመንግስት እውቅና ውጭ ከቦታ ቦታ ለጥፋት የመንቀሳቀስ፣ በሰርግ፣ በለቅሶና በክብረ-በአል ጥይት መተኮስና ህብረተሰብን ማሸበር በፍፁም የተከለከለ መሆኑንም አስታወቋል።