በአማራ ክልል የኮሌራ ወረሽኝ እየተስፋፋ ነው

ሰኔ ፪ ( ሁለት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በንጹህ መጠጥ ውሃ እና የምግብ መበከል ምክንያቶች የሚከሰተው የኮሌራ ወረሽኝ በደቡብ እና ሰሜን ጎንደር፣ በምእራብ ጎጃም ውስጥ በሚገኙ 12 ወረዳዎች አድማሱን እያሰፋ ነው። እስካሁን ድረስም ከ252 በላይ ነዋሪዎች በአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት መጠቃታቸውን የክልሉ የጤና ቢሮ አስታውቋል።
አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት አተት በመባል በሚታወቀው የኮሌራ በሽታ ተጠቂ የሆኑ 47 ታካሚዎች አልጋ ይዘው በሕክምና ማእከላት ውስጥ እየታከሙ ነው። ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተደጋጋሚ ጊዜያት የኮሌራ ወረሽኝ ቢከሰትም አስቀድሞ የመከላከል ሥራዎች ባለመሰራታቸው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው። በአማራ ክልል ያለው የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲነጻጸር ደካማ በመሆኑ ለወረሽኙ መስፋፋት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል። እስካሁን ድረስ በወረሽኙ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ምንያህል እንደሆኑ ማወቅ አልተቻለም።