በነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ መዝገብ የተከሰሱት ተከሳሾች “ ትገደላላችሁ” የሚል ዛቻ እንደደረሰባቸው ተናገሩ

በነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ መዝገብ የተከሰሱት ተከሳሾች “ ትገደላላችሁ” የሚል ዛቻ እንደደረሰባቸው ተናገሩ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 03 ቀን 2010 ዓ/ም) ችሎቱ የተሰየመው በአቃቢ ህግ ምስክር ላይ ብይን ለመስጠት የነበረ ቢሆንም፣ “ባለው የስራ ሂደትና መዝገቡ ሰፊ ስለሆነ፣ ለዛሬ ሊደርስልን አልቻለም፣ ስለሆነም ለመጨረሻ ግዜ አንድ ቀጠሮ መስጠት ግድ ሆኖብናል” በማለት መሃል ዳኛው ተናግረዋል።
ጠበቆች “እስረኞቹ ያሉበትን ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ አስገብታችሁ አጭር ቀጠሮ ይሰጥልን” በማለት ሲያመለክቱ፣ ተከሳሾች በበኩላቸው “ለምን ትዋሻላችሁ፣ እንዳላችሁት ሳይሰራ ቀርቶ ሳይሆን፣ ትዕዛዝ እስኪሰጣችሁ እየጠበቃችሁ ነው። እኛ እየተሰቃየን ነው ሰብአዊ መብታችን ተጥሷል፣ ጥፍራችን ተነቅሏል፣ ብልታችን ላይ ሃይላንድ ተንጠልጥሏል፣ ይሄ ሁሉ በደል እየደረሰብን እንዴት ለዛሬ አልደረሰም ቀጠሮ እንስጣችሁ ትላላችሁ? እኛ የግፍ እስረኞች ነን። መፈታት እንፈልጋለን። ምስክሮች ምስክር የሰጡበት መንገድ አግባብ አይደለም ስለዚህ ጊዜውን አታርዝሙ አታሰቃዩን በቃ እባካችሁ ክሳችንን አቋርጡ”ብለዋል።
26ኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ቶሎሳ “እኔ ለህይወቴ እየሰጋሁ ነው፣ 12 ሰዎች ተመርጠን ተወስደን ትገደላላችሁ ተብለን ሞታችንን እየጠበቅን ነው። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ በተደጋጋሚ ጊዜ የሞት ማስፈራሪያ እየደረሰን ነው። እኔ ጥፍሬ ተነቅሏል። በድብደባው ምክንያት አከርካሪዬን በጣም እያመመኝ ነው። ሰውን የገደሉት ሳይጠየቁ እኛ የድሃ ልጆች ንብረት አውድማችኋል ተብለን እንሰቃያለን ።ኦፊሰር ግርማ እምትገደልበት ቦታ ትወሰዳለህ ብሎኛል። ይህ ሁሉ እየደረሰብኝ ያለው ኦሮሞ ስለሆንኩ ነው፤ እባካችሁ ከመሞታችን በፊት መፍትሔ ስጡን” ብለዋል።
አቶ ካሣ በበኩላቸው “ኦፊሰር ግርማ እና ኦፊሰር ግዑሽ ዞን 5 ግቢ ውስጥ ለፍተሻ ብለው ገብተው እንገድላችኋለን ብለውን ሞታችንን እየጠበቅን ነው። እነዚህ ሁለት ግለሰቦች ማረሚያ ቤቱ ሲቃጠል ዋና ተዋንያኖች ነበሩ ፤ የነሱን ገመና ለመሸፈን እኛ እንሰቃያለን። እኔ እዚህ ላይ ስናገር እናቴ ትሳቀቃለች ግን አማራጭ ስለሌለኝ እናገራለሁ፤ እኛ የአዲስአበባ ልጆች ነን ብሔር የለንም፤ ብሔራችን ኢትዮጵያዊ ነው፤ በግድ የዚህ ብሔር ናችሁ ተብለን እየተሰቃየን ነው።” ብለዋል።
በድብደባ ብዛት መኮላሸቱን ችሎት ፊት አውልቆ ያሳየው ሶማሊ የሚባለው ተከሳሽ ደግሞ፣ “ ትናንት ቲቪ ላይ እያየን ነበር፣ 9 ገድሎ 19 አቁስሎ በስህተት ነው እያለ እሚዛበት መንግስት ነው ያለው። ስለዚህ እኛንም ከፈለጋችሁ ተሳስታችሁ ካለበለዚያ አውቃችሁ ግደሉን፤ እባካችሁ አታሰቃዩን፤ በቃ ግደሉን ወይ አስገድሉን” ብሎአል።
አቶ አጥናፉ የተባሉት ተከሳሽ በበኩላቸው “ይህን ያህል ግዜ እዚህ ችሎት የተመላለስኩት ፍትህ ከእናንተ አገኛለሁ ብዬ ሳይሆን ከግዜ ብዛት ከመሃላችሁ አንድ ህሊና ያለው ሰው ይኖራል ብዬ ነው፤ ነገር ግን ሁላችሁም አንድ ናችሁ፤ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ እዚህ ችሎት ላይ አልገኝም፤ ፍርዳችሁን እዛው ላኩልኝ፤ ከገደሉኝም ደስ እያለኝ ነው እምሞተው። ስለ እናት ሀገሬ ስል ደስ እያለኝ እሞታለሁ።” ብለዋል።
የተከሳሽ ጠበቆችም እነዚህ ማስፈራሪያ እያደረሱ ላሉ ሃላፊዎች ትዕዛዝ ይሰጥልን እና ችሎት ፊት ቀርበው ይጠየቁ፣ ደንበኞቻችን ህይወታችን አደጋ ላይ ነው ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል።
መሃል ዳኛው አቤቱታችሁን በፅሁፍ አቅርቡና ውሳኔ እንሰጥበታለን ብለዋል። ችሎቱ ብይን ለመስጠት ለሚያዚያ 16 ቀን 2010 ኣም መቀጠሩንም ተናግረዋል።