በነቀምትና ደምቢዶሎ የግንቦት20 ቲሸርት ሳይከፋፈል ቀረ

ግንቦት ፳፬ ( ሃያ አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢህአዴግ ግንቦት20ን ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀውን ግንቦት 20 ቲሸርት ወለጋ ነቀምት ላይ ለመሸጥ ሙከራ ሲያደርግ ህዝቡ “ የደም ቲሸርት ነው ወይ የምንገዛው? “ በማለት ለመግዛት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። የህዝቡን ሁኔታ ያዩት ካድሬዎች፣ ህዝቡ ቲሸርቱን በነጻ እንዲወስድ ቢጠይቁም፣ “ የልጆቻችንን ደም አንለብስም፣ የተደረገብንን አንረሳም፣ ድርጊታችሁ የኦሮሞን ህዝብ እንደመናቅ፣ እንደመድፈር ይቆጠራል” የሚሉና ሌሎችንም ሃይለቃል የተሞላባቸውን ቃላት በመናገር ቲሸርቱን እንደማይገዙትና እንዲያቃጥሉት ነግረዋቸዋል።
በድርጊቱ የተበሳጩት ካድሬዎች ቲሸርቶችን ጭነው ወደ ደንቢዶሎ የሄዱ ሲሆን፣ የነቀምት ነዋሪዎች ደምቢዶሎ ለሚኖሩ ሰዎች አስቀድመው ስልክ በመደወልና መልእክት በማስተላለፋቸው፣ ካደሬዎቹ በደምቢዶሎም ተመሳሳይ ተቃውሞ አጋጥሟቸዋል።
በክልሉ በሽያጭ እንዲከፋፈሉ የተላኩ የግንቦት 20 ቲሽርቶችን መግዛት ቀርቶ በነጻ የሚቀበል ሰው መጥፋቱን ወኪላችን ዘግቧል።
ገዢው ፓርቲ ስልጣን በአፈሙዝ የያዘበትን 26 ዓመት በአል በተቀዛቀዘ ስሜት አክብሯል። በአማራ እና በኦሮምያ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ተቃውሞ እንዲሁም በመላ አገሪቱ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በህዝቡ ውስጥ ያለው ስሜት እንዳለ መሆን ገዢው ፓርቲ አመቱን በቀዘቀዘ ስሜት እንዲያከበር ሳያስገድደው እንደማይቀር ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።