በታንዛኒያ ውቂያኖስ ዳርቻ በጀልባ ሲጓዙ የነበሩ ሰባት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ተገልብጠው ህይወታቸውን አጡ።

በታንዛኒያ ውቂያኖስ ዳርቻ በጀልባ ሲጓዙ የነበሩ ሰባት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ተገልብጠው ህይወታቸውን አጡ።
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 16 ቀን 2011 ዓ/ም ) መነሻቸውን ከኬኒያ በማድረግ ወደ ደቡብ አፍሪካ በመጓዝ ላይ ከነበሩት 13 ተጓዦች ውስጥ ባጋጠማቸው የጀልባ መገልበጥ አደጋ ሰባቱ መሞታቸውን ማክሰኞ ዕለት የታንዛኒያ ፖሊስ አስታውቋል።
ጀልባዋ ሰኞ ማለዳ ላይ ህንድ ውቅያኖስ የኬኒያ እና የታንዛኒያ የባህር ዳርቻ በጀልባ ጉዞዋቸውን በማድረግ ላይ እያሉ አደጋው እንዳጋጠማቸው የአገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል።
የታንጋ ግዛት ፖሊስ ኮማንደር ኤዲዋርድ ኩሞንቤ እንዳሉት ”ከተጓዦቹ መሃከል12ቱ ኢትዮጵያዊያን ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ አንዱ የሌላ አገር ዜጋ ያለው የጀልባዋ ካፒቴን ነበር። ዜግነቱን ግን ማረጋገጥ አልቻልንም። ምክንያቱም እስካሁን ድረስ አልተያዘም። ሰባቱ ወዲያውኑ ሲሞቱ አምስቱ በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት ደርሶባቸዋል። አድራሻውን አጥፍቶ የተሰወረውን ካፒቴን ለመያዝ ፖሊስ አሰሳውን አጠናክሮ ቀጥሏል።” ሲሉ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
የታንዛኒያ የስደተኞች ቢሮ የሟቾቹን ኢትዮጵያዊያን የቀብር ስነስርዓት አፈጻጸም ከኢትዮጵያ ኤንባሲ ጋር በጋራ በመተባበር ለማስፈጸም እንቅስቃሴ መጀመሩን ዴይሊ ኔሽን ዘግቧል።
በተያያዥ 20 ህገወጥ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ በታንዛኒያ አቆራርጠው ሲገቡ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ካለ ህጋዊ ፍቃድ መግባታቸውን ተከትሎ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንደሚታይ ፖሊስን ጠቅሶ ኒውስ አፍሪካ ዘግቧል።
ከኬንያ ሞምባሳ ተነስተው ወደ ታንዛንያ በጀልባ በመጓዝ ላይ እያሉ በደረሰ የመስጠም አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ስምንት ኢትዮጵያውያንን አስከሬን ወደ አገር ቤት ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ዛሬ አስታውቋል።
የኬኒያው ዴይሊ ኔሽን ሰባት ኢትዮጵያዊያን መሞታቸውን ሲገልጽ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር በበኩሉ ቁጥራቸውን ስምንት አድርሶታል። አንዱ ሟች ኢትዮጵያዊ ከጉዳተኞቹ መሃክል ይሁን አይሁን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።