በቱርክ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ተቋም በኢትዮጵያ ያቋቋማቸው ት/ቤቶች ለቱርክ መንግስት ተላልፈው እንዲሰጡ ጥያቄ ቀረበ

ኢሳት (ጥር 2 ፥ 2009)

ቱርክ በሽብርተኛ ድርጅት የፈረጀችው አንድ ተቋም (ድርጅት) በኢትዮጵያ ያቋቋማቸው ትምህርት ቤቶች ለቱርክ መንግስት ተላልፈው እንዲሰጡ ሃገሪቱ ይፋዊ ጥያቄ አቀረበች።

የቱርክ ባለስልጣናት በዚሁ በአሜሪካን በጥገኘት የሚገኙትን የተቋማት ፓርቲ አመራር ፋቱላህ ጉለንን እንዲሁም ያቋቋማቸው በርካታ ድርጅቶችን በሽብርተኛ ተቋም በመፈረጅ የተቃዋሚ አመራሩን ለፍርድ እንደምትፈልጋቸው ስትገልፅ  መቆየቷ ይታወሳል።

የጉለን ንቅናቄ ተብሎ በሚጠራው በዚሁ ድርጅት የተቋቋሙ ስድስት ትምህርት ቤቶች ክጥቂት አመታት በፊት በአዲስ አበባ ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ አናዱሉ የተሰኘ የቱርክ የዜና አውታር ማክሰኞ ዘግቧል።

የትምህርት ቤቶቹን ህጋዊነት በተመለከተ በቅርቡ በአዲስ አበባ ጉብኝት ያደረጉ የቱርክ ባለስልጣናት ጉዳዩን አንስተው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መወያየታቸው ታውቋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያን የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ሃገራቸው ስድስቱ ትምህርት ቤቶችን ለቱርክ መንግስት አስተላልፎ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ይፋ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ በሰፊ የኢንቨስትመንት ስራ ላይ ተሰማርታ የምትገኘው ቱርክ  በጉለን ንቅናቄ የተቋቋሙት ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ አልያም ተላልፈው እንዲሰጧት ጥያቄ ማቅረቧን ለመረዳት ተችሏል።

ትምህርት ቤቶቹ የስራ ሂደታቸው እና የተማሪዎቹ የትምህርት ሂደት በማይጎዳ ሁኔታ ህጋዊ መንገድን በተከተለ አሰራር ለቱርክ መንግስት ተላልፈው እንደሚሰጡ አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ለአናዱሉ የዜና አውታር አስታውቀዋል።

ትምህርት ቤቶቹ ከመነሻውም ቢሆን በቱርክ መንግስት ድጋፍ በኢትዮጵያ ሊቋቋሙ መብቃታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል።

ይሁንና ከሁለት ሳምንት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝትን ያደረጉ የቱርክ የኢኮኖሚ ሚኒስትር ኒሃት ዜይቤኪ ትምህርት ቤቶቹ ባለቤትነታቸው የጉለን ንቅናቄ መሆኑ ቀርቶ ለቱርክ መንግስት ተላልፈው እንዲሰጡ በይፋ መጠየቃቸውን የቱርክ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የቱርክ ባለስልጣናት በዚሁ በአሜሪካ በጥገኝነት የሚገኙት የንቅናቄው አመራር ፍቱላህ ጉለን ከወራት በፊት በሃገሪቱ ተሞክሯል የተባለውን የመፈንቅለ መንግስት ድርጊት እንዳቀነባበሩ ይገልጻሉ።

በጉለን የሚመሩ የተለያዩ ድርጅቶች በቱርክ በሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን ፖሊስ፣ ጦር ሰራዊትና የፍትህ ስርዓት ውስጥ ሰርግው በመግባት የሃገሪቱን መንግስት ለመጣል ሙከራን እንደሚያደርጉ ቱርክ ስትገልፅ መቆየቷ ይታወሳል።

በጉለን ንቅናቄ ተከፍተዋል በተባሉትና በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ስድስት ትምህርት ቤቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።