በባለስልጣናት የውጭ አካውንቶች ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ዶ/ር አብይ ተናገሩ

በባለስልጣናት የውጭ አካውንቶች ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ዶ/ር አብይ ተናገሩ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 07 ቀን 2010 ዓ/ም) ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለተሰበሰቡ የተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በአሰራራቸው ዙሪያ በሰጡት መግለጫ በውጭ አገራት ባንኮች የባንክ ሂሳብ ደብተር ያላቸው ባለስልጣናት ምርመራ እየተደረገባቸው ነው።
የካቢኔ ስብሰባቸውን ከአርብ ወደ ቅዳሜ እንደተለወጠና ጊዜን በስራ ሰዓት በስብሰባ ማባከን እንደሚያስቀር ተናግረዋል።
ባለስልጣናት አሰራራቸውን ከህዝብ ሳይደብቁ መረጃ እንዲሰጡ የተናገሩት ዶ/ር አብይ፣ አገሪቱ እስከዛሬ የመጣችበት መንገድ የህዝቡን ጥያቄ መመለስ የማይችል በመሆኑ ሊቀየር ይገባል።
ዶ/ር አብይ ለአዲሱ አሰራር አይመጥኑም ያላቸውን ነባር የመንግስት አመራሮች በጡረታ ማሰናበታቸውንም አስታውቀዋል። ከተሰናበቱት መካከል የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት አቶ ስብሃት ነጋ፣ የፖለሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዶ/ር ካሱ ኢላላ፣ ከተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም፣ ዕቅድና ፖሊሲ ዝግጅት ፕሮጀክት አቶ በለጠ ታፈረ፣ በንግድና ኢንዱስትሪ የፖሊሲ ዕቅድ አፈጻጸምና ክትትል ሃላፊ አቶ ታደሰ ኃይሌ እንዲሁም ፣ከፖሊሲ ምርምር ማዕከል አቶ ማን ያዘዋል መኮንን ተነስተዋል።