በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች ዛሬ የተቃውሞ ሰልፎች ተደረጉ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 1/2010)በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች ዛሬ የተቃውሞ ሰልፎች ተደረጉ።

ሶስት ሰዎች በመንግስት ታጣቂዎች መገደላቸውም ታውቋል።

በአምቦ፣ ሻሸመኔ፣ ነቀምት፣ አዳባ፣ ኮፈሌና በሀረርጌ የተካሄዱት ሰልፎች የስርዓት ለውጥ በሚጠይቁ መፈክሮች የታጀቡ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የጠየቀው ህዝብ የህወሀት መንግስት ከስልጣን እንዲወርድ በከፍተኛ የተቃውሞ እንቅስቃሴ መጠየቁንም ለማወቅ ተችሏል።

የሻሸመኔው ተቃውሞ ከበድ ያለ፡ እንደወትሮውም የመንግስት ታጣቂዎች ጭካኔ የታየበት ነበር።

ሻሸመኔ በዛሬው ተቃውሞ በከፍተኛ የህዝብ ብዛት መንገዶቿ ተጥለቅልቀው መዋላቸው ታውቋል።

ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማምሻው ድረስ በዘለቀው በዚሁ የሻሸመኔ ተቃውሞ ጸረ ህወሀት መልዕክቶች የተላለፉ ሲሆን የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተኩስ መክፈታቸውን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

እስካሁን ባለው መረጃ በሻሸመኔ የመንግስት ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት አራት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከ20 የማያንሱ ተማሪዎች መጎዳታቸው ታውቋል።

ከተለያዩ አካባቢዎች ወደሻሸመኔ የሚያስገቡና የሚያስወጡ መንገዶች ተዘግተው የዋሉ ሲሆን ከሀዋሳ ወደ ሻሸመኔ ሲያቀኑ የነበሩ ተሽከርካሪዎች እንዲመለሱ መደርጋቸውም ተገልጿል።

በአምቦ ዛሬ ቤቱ የቀረ ነዋሪ አልነበረም። ላለፉት ሁለት ዓመታት ተቃውሞ ተለይቷት የማያውቀው አምቦ ቀድሞ ያልተመለሱ፡ አዲስ የተጨመሩ ጥያቄዎችን ባነገቡ ነዋሪዎቿ ድምጽ ደምቃ ነበር የዋለችው።

በእስር ላይ የሚገኙት የኦፌኮ መሪዎች የአንዳቸውም ስም አልቀረም። መረራ ይፈቱ፣ በቀለ ገርባ ጀግናችን፣ አዲሱ ቡላላ መሪያችን የሚለው የአምቦዎች ድምጽ በዋነኛው መልዕክቱ ታጅቦ ሲሰማ ነው የዋለው።

ዋነኛው መልእክቱና ከፍ ብሎ የተሰማው መፈክር ‘’የወያኔ መንግስት በቃን’’ የሚለው እንደነበረ በቪዲዮ ከተሰራጨው የተቃውሞ ምስል ለመረዳት ተችሏል።

ባለፈው የእሬቻ በዓል በሰላም ተከብሮ ከተጠናቀቀና በቡራዩ በተመሳሳይ የበዓል ትዕይንት ለህወሀት መንግስት ግልጽ መልዕክት ከተላለፈ ወዲህ ዛሬ በአምቦና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የተደረጉት የተቃውሞ ትዕይንቶች ህዝቡ ጥያቄው ሳይመለስ መቼም እረፍት እንደማይኖረው ያመላከቱ ናቸው ተብሏል።

ተቃውሞው ከአምቦና ሻሸመኔ በተጨማሪ በኮፈሌና አዳባ የተካሄደ ሲሆን በወለጋ በተለያዩ ከተሞችና የቀበሌ መንደሮች ህዝብ አደባባይ በመውጣት ቁጣና ብሶቱን አሰምቷል።

በሀረርጌም በበርካታ ከተሞች በተካሄደው ተቃውሞ ተመሳሳይ መልዕክቶች የተላለፉ ሲሆን በመንግስት ታጣቂዎች እርምጃ በርካታ ሰዎች መጎዳታቸው ታውቋል።

የተገደሉ ሊኖሩ እንደሚችሉ የጠቀሱት ምንጮች የዛሬው ተቃውሞ መንግስት አሁንም ከመግደል ውጭ ለህዝብ ጥያቄ ሌላ ምላሽ እንደሌለው ያስመሰከረበት ሆኗል ብለዋል።

የዕለቱ ተቃውሞ የታሰሩ ፖለቲከኞች እንዲፈቱ፣ የኦሮሞ ተወላጆች መፈናቀል እንዲቆም፣ የአጋዚ ወታደሮች ከአካባቢያችን ለቀው ይውጡ የተሰኙ መልዕክቶች የተሰሙ ሲሆን በግንባር ቀደምትነት የተላላፈው መልዕክት ግን አንድ ነው። የወያኔ መንግስት ይውረድ!