በቀብሪ ደሃር እስር ቤት ውስጥ በስቅላት የተገደለችውን የ24 አመቷ ወጣት ሞት ለማስተባበል እየተሞከረ ነው

በቀብሪ ደሃር እስር ቤት ውስጥ በስቅላት የተገደለችውን የ24 አመቷ ወጣት ሞት ለማስተባበል እየተሞከረ ነው
(ኢሳት ዜና ግንቦት 06 ቀን 2010 ዓ/ም) ዘመዶችሽ እኔን ሊከሱ ወደ አዲስ አበባ ሄደዋል በሚል ምክንያት በኢትዮ-ሶማሊ ክልል መሪ በአቶ አብዲ ኢሌ ወታደሮች በቀብሪ ደሃር እስር ቤት ውስጥ ባለፈው ሃሙስ በስቅላት የተገደለችው የ24 አመቷ ወጣት ታሲር ኦማር ፎድን ግድያ ለማስተባበል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። ወጣቷ ከተገደለች በሁዋላ ዘመዶቿ ወደ እስር ቤት ተጠርተው ወጣት ታሲር ራሷን እንዳጠፋች እንዲፈርሙ ቢጠየቁም፣ ቤተሰቦቿ ግን አንገቷ አካባቢ የሽቦ ምልክትና ሌሎችንም ሁኔታዎች በማየታቸው አንፈርም ማለታቸውን ምንጮቸ ገልጸዋል።
መረጃው የደረሰው የከተማው ህዝብ ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞውን ሲገልጽ ወታደሮች በህዝቡ ላይ በቀጥታ በመተኮስ ጉዳት አድርሰዋል። ነዋሪዎች በፖሊስ ጣቢያው ላይ ድንጋይ በመወርወር ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል። እስካሁን ባለው መረጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል። ከ60 በላይ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። ወጣቷ በተያዘች በሰዓታት ውስጥ መገደሉዋን የሚገልጹት ምንጮች፣ ድርጊቱ ብዙ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል።
የአብዲ ኢሌ አገዛዝ ወጣቷን በስውር የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ድርጅት አባል አድርጎ እያቀረባት ቢሆንም፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን የሚቀበሉት አልሆነም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የክልሉ ነዋሪዎች በአብዲ ኢሌ አገዛዝ ላይ ጠንካራ ተቃውሞ በማሰማት ላይ ናቸው።
የህወሃት ድጋፍ እንዳለው የሚነገርለት አብዲ ኢሌ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን መግደሉን፣ በሺዎች የሚቆጠሩትን ማሰሩ፣ ለስደት መዳረጉን እንዲሁም ከ800 ሺ ያላነሱ የኦሮሞ ተወላጆችን ቢያፈናቅልም እስካሁን ለፍርድ አልቀረበም።