በሶማሌ ክልል የጅምላ መቃብሮች ፍለጋ ተጠናቀቀ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 13/2011)በሶማሌ ክልል ባለፉት 10 ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለው የተቀበሩባቸው የጅምላ መቃብሮች ፍለጋ መጠናቀቁን የክልሉ መንግስት አስታወቀ።

የክልሉ መንግስት ይፋ እንዳደረገው መረጃም የጅምላ መቃብሮቹን አጠቃላይ መረጃም ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በሶማሌ ክልል ተገድለው በጅምላ የተቀበሩበትን የ200 ሰዎችን የምርመራ ሒደት ማጠናቀቁን ፖሊስ አስታውቋል።

የተገደሉት ዜጎች በቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ የስልጣን ዘመን የጸረ ሰላም ሃይሎች በሚል የተወነጀሉ መሆናቸውን ፖሊስ ለችሎት ባቀረበው የምርመራ ሪፖርት ላይ አመልክቷል።

ፖሊስ ተጨማሪ የተገደሉ ሰዎችን የተመለከተ ምርመራ ለማድረግ ወደ ጂጂጋ እንደሚያመራ በመግለጽ 14 ቀናት ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ለችሎቱ ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል።

ዛሬ በችሎት የቀረበው የፖሊስ የምርመራ ሪፖርት እንደሚያመልክተው ከ2004 ዓመተምህረት ጀምሮ በክልሉ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ 200 ሰዎች በአንድ ላይ የተቀበሩበት የጅምላ መቃብር ጉዳይ ተጠናቋል።

መርማሪ ፓሊስ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ የአራት ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ እየተመለከተ ላለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የወንጀል ችሎት ይህንኑ የምርመራ ውጤቱን አቅርቧል።

እነዚህ የተገደሉት 200 ሰዎች የክልሉን አሰራር ክፍተትን የተቃወሙ መሆናቸውን የጠቀሰው የምርመራ ሪፖርቱ የፀረ ሰላም ኃይሎች ተብለው መገደላቸውን አርጋግጫለሁም ብሏል።

ለሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት በጅምላ ተቀብረዋል የተባሉት የ200 ሰዎች ጉዳይ አላስገረማቸውም።

በቅርቡ ስልጣን የያዙት አቶ ሙስጠፋ ዑመር እንደሚሉት ከ10ሺህ በላይ ዜጎች ተገድለው የተቀበሩባቸው በርካታ የጅምላ መቃብሮች የተገኙ በመሆናቸው የ200ዎቹ አዲስ አልሆነባቸውም።

አቶ ሙስጠፋ ዑመር የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ለኢሳት በሰጡት ቃለመጠይቅ በተለያዩ የክልሉ አከብባቢዎች የጅምላ መቃብሮችን የማፈላለጉ ስራ እየተጠናቀቀ ነው።

ባለፉት 10 ዓመታት የተገደሉት ጅጂጋን ጨምሮ በዋና ዋና የክልሉ ከተሞች በተቆፈሩ ጉድጓዶች በጅምላ ተቀብረዋል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የወንጀል ችሎት የቀረበው የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ላይ እንደተመለከተው በጅምላ የተቀበሩት ሰዎች የተገደሉት የክልሉን አስተዳደር በመንቀፋቸውና በመተቸታቸው ነው።

አቶ ሙስጠፋ ዑመር የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ለኢሳት እንደገለጹትም ዜጎች በክልሉ ሲገደሉ የነበሩት ጸረ ሰላም ሃይሎች እየተባሉ ነው።

ከአንድ ቤተሰብ ዘጠኝ ሰዎች የተገደሉ መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ።

በሶማሌ ክልል የተገኙትና ከ10ሺህ በላይ ዜጎች በጅምላ የተቀበሩባቸው መቃብሮችን በተመለከተ ምርመራው ተጠናቆ ለሚመለከተው አካል እንድሚቀርብም አቶ ሙስጠፋ ገልጸዋል።

ተጨማሪ የጅምላ መቃብሮች ሊኖሩ እንደሚችሉና በቀጣይ የማፈላለግ ስራ እንደሚከናወንም አቶ ሙስጠፋ ይናገራሉ።