በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ድንበር አካባቢ ዳግም ግጭት ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 15/2010)ጋብ ብሎ የነበረው በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ድንበር አካባቢ ዳግም ግጭት ተቀሰቀሰ።

በሞያሌ አቅራቢያ ቦርቦር በተባለው አካባቢ በተቀሰቀሰው በዚሁ ግጭት ከሁለቱ ወገኖች 27 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።

የህወሃት ልዩ ኮማንዶ በአካባቢው ከገባ በኋላ ግጭቱ እንደተቀሰቀሰ የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች በግድያው ላይ የኮማንዶ ሃይሉ በቀጥታ መሳተፉንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በአርሲ ነገሌ የመንግስት ካድሬዎች አቀናብረውታል በተባለ ጥቃት በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የኢሳት ምንጮች ከላኩት መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

በአቅራቢያው የመከላከያ ሰራዊት የሚገኝ ቢሆንም ሊያስቆም እንዳልቻለ ተገልጿል።

ከግማሽ ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን ለተፈናቀሉበት፣ በመቶዎች ለሚቆጠሩት መገደል ምክንያት የሆነው በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች መሀል የተፈጠረው ግጭት ያዝ ለቀቅ እያደረገው ቀጥሎ ሰሞኑን በሞያሌ አከባቢ መባባሱን ነው የኢሳት የመረጃ ምንጮች የገለጹት።

በሞያሌ አቅራቢያ ቦር ቦር በተባለ ስፍራ ከሁለት ሳምንት በፊት የህውሃት ልዩ ሃይል መስፈሩን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ግጭት ይህው የህወሃት ጦር ዋነኛ ተሳታፊ እንደሆነም ታውቋል።

ልዩ የኮማንዶ ሃይሉ በካባቢው የሰፈረበት ምክንያት ባይታወቅም ወዲያኑ የወሰን ግጭት ተቀስቅሶ በርካታ ሰዎች መሞታቸውና የህወሃት ልዩ ወታደሮች ከገቡ በኋላ እንደአዲስ በተጀመረው ግጭት የ27 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል።

ኢሳት ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ እንደሚሉት እንደአዲስ በተቀሰቀሰው ግጭት ውስጥ የህወሃት ልዩ ኮማንዶ ሚና ከፍተኛ ነው።

ግጭቱን ሰበብ አድርገው የልዩ ኮማንዶው አባላት በአካባቢው ያገኙትን ሰው መግደላቸው ተገልጿል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ግጭቱ አለመብረዱም ታውቋል።

በሌላ በኩል ዛሬ በአርሲ ነጌሌ በተቀሰቀሰ ግጭት ከፍተኛ የንብረት ውድመት መከሰቱ ተገለጿል።

የእርስ በርስ ግጭት እንዲሆን ታቅዶ በመንግስት ደህንነቶች የተጫረውንና የአንድ ሰው ህይወት መጥፋቱን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ግጭት ብሄርን መነሻ ባደረገ መልኩ ከፍተኛ የንብረት ውድመት መከሰቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

ሰሞኑን በዝዋይ በተመሳሳይ በወላይታ ብሄር ተወላጆች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ያስታወሱ ወገኖች በአርሲ ነገሌም የእርስ በእርስ ግጭት ለማስነሳት በመንግስት ደህንነቶች እንቅስቃሴ መደረጉ ታውቋል።

በአቅራቢያ የነበረው የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ በርካታ ንብረቶች ከወደሙ በኋላ ዘግይቶ መድረሱን የጠቀሱት ነዋሪዎች አሁን በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ሆነው በቤታቸው ለመቀመጥ መገደዳቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ዘንዘልማ ካምፖስ የግብርና ትምህርት ክፍል ውስጥ ብሄርን መነሻ ያደረገ ግጭት ተፈጥሮ ጉዳት የደረሰ ሲሆን በአንድ ተማሪ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉ 5 ከትግራይ ክልል የመጡ ተማሪወች በ5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑ ታውቋል።