በሱዳን የተቃዋሚ ፓርቲዎችና ማህበራት ተቃውሞውን መደገፋቸው ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 24/2011) በሱዳኑ ፕሬዝዳንት ጄኔራል ኦማር አልበሽር ላይ የተጀመረውንና ሁለት ሳምንት ያስቆጠረውን ተቃውሞ 22 ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ማህበራት መደገፋቸው ታወቀ።

22ቱ የሱዳን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፕሬዝዳንት አልበሽር ስልጣን እንዲለቁና የሽግግር መንግስት በአስቸኳይ እንዲመሰረትም ጥሪ አቅርበዋል።

ፋይል

ፕሬዝዳንት አልበሽር በበኩላቸው በችግሩ ዙሪያ መርማሪ ኮሚቴ አዋቅረዋል።

ራሳቸውን የለውጥ ብሔራዊ ህብረት በማለት የሰየሙት 22 ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ማህበራት ትላንት ማክሰኞ በይፋ ባደረጉት ጥሪ ፕሬዝዳንት አልበሽር ስልጣናቸውን ለሃገሪቱ ሉዓላዊ ካውንስል እንዲያስረክቡና የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ጠይቀዋል።

የሽግግር መንግስቱም ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የሚካሄድበትን ቀን እንዲወስንም ጥሪ አቅርበዋል።

በሐገሪቱ የተፈጠረውን የኢኮኖሚ ቀውስ መንግስት ሊፈታው አይችልም ቀውሱ በዋናነት የፖለቲካ ችግር ነጸብራቅ ነውና ያሉት 22ቱ ድርጅቶች መፍትሔው የጄኔራል አልበሽር መንግስት ስልጣን መልቀቅ ብቻ ነው ሲሉ አሳስበዋል።

በ22ቱ ድርጅቶችና ማህበራት የቀረበውን መፍትሔ አለመቀበል ሱዳንን ወደ አስከፊ ቀውስ ይወስዳታል ሲሉም ለፕሬዝዳንት አልበሽር ማሳሰቢያቸውን አስገብተዋል።

በሱዳን ውስጥ ሁለት ሳምንታት ባስቆጠረው ተቃውሞ መንግስት 19 ሰዎች መገደላቸውን ሲገልጽ አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ደግሞ 37 ሰዎች መሞታቸውን የሚያሳይ ሪፖርት ደርሶኛል ብሏል።

የሱዳን መንግስት ተቃውሞውን ከእስራኤል መንግስት ጋር በማያያዝ የታሰሩ ወጣቶችን በቅጥረኝነት ወንጅለው በቴሌቪዥን ቢያቀርቡም ተቃውሞው ግን ቀጥሏል።

ፕሬዝዳንት አልበሽር ዘግይተዋል ቢባሉም በፍትህ ሚኒስትሩ የሚመራ መርማሪ አካል መሰየማቸው ታውቋል።

ነጻነቷን ካገኘች በዚህ ሳምንት 63 አመት ያስቆጠረችው ሱዳን 29 አመት በፕሬዝዳንት አልበሽር አገዛዝ ውስጥ ቆይታለች በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዙት ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር የመጣባቸውን ወጀብ መሻገር ከቻሉና ሰኔ ላይ ከደረሱ ስልጣን የያዙበትን 30ኛ አመት ያከብራሉ ተብሎ ይታሰባል።