በሱዳን ወደ ወህኒ የተጋዙ ሰዎች እንዲፈቱ ተጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 30/2011)በሱዳኑ ፕሬዝዳንት ጄኔራል ኡመር አልበሽር ላይ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ወደ ወህኒ የተጋዙ ሰዎች እንዲፈቱና አልበሽር ከስልጣን እንዲወርዱ የካርቱም ነዋሪዎች ጠየቁ።

ዛሬ ሱዳን ርዕሰ መዲና ካርቱም አደባባይ የወጡት በሲዎች የሚቆጠሩት የካርቱም ነዋሪዎች ጄኔራል አልበሽር ከስልጣን እንዲወርዱ መጠየቃቸው ተሰምቷል።

ነጻነት፣ሰላምና ፍትህ የሚሉ መፈክሮችን ማስተጋባታቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስን ጠቅሶ ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል።

“ወታደሮችህን በሙሉ አሰማራ መውደቅህ ግን አይቀርም”በማለት ለጄኔራል አልበሽር መልዕክት ያስተላልለፉት ሰልፈኞች በካርቱም ማዕከላዊ የገበያ ስፍራ ሲንቀሳቀሱ ታይቷል።

አድማ በታኝ ፖሊሶች አስለቃሽ ጋዝ በመርጨት ሰልፈኞቹን ለመበተን መሞከራቸውንም ዘገባው አመልክቷል።