በሱልልታ ከተማ ነዋሪዎች በስጋት እና በሰቆቃ እየኖሩ መሆናቸውን ገለጹ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 6/2011) በኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ አቅራቢያ የምትገኘው ሱልልታ ከተማ በ7 ቀናት ውስጥ ቤታችሁ ይፈርሳል የተባሉ ነዋሪዎች በስጋት እና በሰቆቃ እየኖሩ መሆናቸውን ገለጹ።

የሱልልታ እና የአካባቢው  ነዋሪዎች  የኦሮሚያ ክልል መንግስት ቤታችን ሊያፈርስ ቀይ ምልክት አስምረውብናል፥ ከመፈናቀላችን በፊትም ድረሱልን ሲሉ ጥሪ አሰምተዋል ፡፡

የጎረቤቶቻችን እና የአንዳንዶችን ቤት ግን ለይተው ትተውታል ሲሉም ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

በሱልልታ ከተማ አስተዳደር ለቤቶቹ መፍረስ የተሰጠው ምክንያት አካባቢው የመንገድ ግንባታ የሚካሄድበት ነው በሚል እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች አስታውቀዋል።

ቤታቸው ላይ ምልክት የተደረገባቸው የሱልልታ ከተማ ነዋሪዎች ተሰባስበው የአካባቢውን አስተዳደር ሊያነጋግሩ ቢሄዱም ከንቲባዋ ወይዘሮ ሮዛ ኡመር ግን ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

ለሸገር ሬዲዮ እሮሮአቸውን ያሰሙት የሱልልታ ነዋሪዎች ለፍተን ጥረን ያፈራነው ሀብታችን ሳይበተን ድረሱል ሲሉ ተማጽነዋል።

ከንቲባዋ ወይዘሮ ሮዛ ኡመር ቤት ይፈርሳል የሚባለው ሐሰት ነው፤ ሕጋዊ ስለመሆናችሁ ማስረጃችሁን አቅርቡልን ነው ያልነው ሲሉ ለሸገር ሬዲዮ ገልጸዋል፡፡ ባንዱ ላይ ምልክት አድርገን በሌላው ላይ የምንተውበት ምክንያት የለም ሲሉም አክለዋል፡፡

በቅርቡ በለገጣፎ ሕገ ወጥ ግንባታ በሚል በለገጣፎ እንዲሁም በሰበታና በሌሎችም የኦሮሚያ የአዲስ አበባ አዋሳኝ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸውና ሰብአዊ ቀውስ መከሰቱ ይታወሳል።

የኦሮሚያ ክላልዊ መንግስትም ሕገወጥ ግንባታን ለመከላከል ቤት የማፍረሰ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋጋጡ ይታወሳል።