በሞያሌ በትንሹ 12 ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 9/2011) በሞያሌ በሚገኘው የበቀለ ሞላ ሆቴል ላይ በተፈጸመ ጥቃት በትንሹ 12 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።

ጥቃቱ የተፈጸመው የቦረና ኦሮሞና የሶማሌ ገሪ ብሄረሰብተወካዮች ከፌደራል መንግስቱ ሰራዊት አመራሮች ጋር ውይይት እያደረጉ በነበረ ጊዜ መሆኑን አዲስ ስታንዳርድ የተሰኘ የዜና ምንጭእማኞቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

በጥቃቱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መሳተፋቸውም ተገልጿል። በሞያሌ ሳምንቱን በደፈነውና እንደአዲስ ባገረሸው ግጭት ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውም ታውቋል።

የሞያሌው ግጭት መነሻው በ1997 የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ እንደሆነ በሁለቱም ወገኖች ይገለጻል።

በህዝበ ውሳኔው መሰረት ሁለቱ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው የሞያሌ ወረዳ አካባቢዎች ውስጥ ያሉ ቀበሌዎች ላይ የይገባኛል ጥያቄ ተነስቶ ከ10 ዓመታት በላይ ቀጠናው ከውዝግብ ተለይቶ አያውቅም።

ህዝበ ውሳኔ ያልፈታው ውዝግብን በሃይል እልባት እንሰጠዋለን በሚል በሁለቱ ወገኖች ታጣቂዎች መካከል ያዝ ለቀቅ ሲያደርገው የነበረው ግጭት ባለፉት ስምንት ወራት ከፍተኛ የሰው ልጅ ሰብዓዊ ቀውስ የተከሰተበትን ዕልቂት አስከትሏል።

ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ እንደአዲስ ባገረሸው በዚሁ ግጭት በትንሹ ከ50 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

በስምንት ወራቱ ግጭት ከሶማሌ ክልል ብቻ 600 ሺህ ዜጎች መፈናቀላቸው ታውቋል።

አዲስ ስታንዳርድ የተሰኘው የዜና ምንጭ እማኞቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ደግሞ የቀውስ ቀጠና በሆነችው የሞያሌ ከተማ በሚገኝ የበቀለ ሞላ ሆቴል ላይ ጥቃት ተፈጽሞ ከ12 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

እንደዘገባው ከሆነ የሁለቱ ክልሎች የጸጥታ ቢሮ አመራሮች፣ የሁለቱ ብሄረሰቦች ተወካዮችና የመከላከያ ሰራዊት ሃላፊዎች የተገኙበት ስብስባ እየተካሄደ ነበር።

በጥቃቱ ስብሰባው ላይ በነበሩ አመራሮች ላይ ጉዳት ስለመድረሱ የተገለጸ ነገር የለም። ጥቃቱን በመፈጸሙ በኩል የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንዳሉበት ነው የተገለጸው።

ትላንት ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት በተመለከተ ከሁለቱም ክልሎች አመራሮች መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

አዲስ ስታንዳርድ እንዳለው የተኩስ ልውውጥ ከጥቃቱ በኋላም ቀጥሎ ውሏል።

ኢሳት ያነጋገራቸው የሶማሌ ክልል የጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዲ አዲል ግጭቱን የሚያባብሱት በአካባቢው የሚገኙ የሁለቱም ክልል መዋቅር አመራሮችና ኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ናቸው ብለዋል።

የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት የፌደራል መንግስቱ የአካባቢውን የጸጥታና ደህንነት ቁጥጥር ከሁለቱም ወገኖች እጅ በመውሰድ መቆጣጠር ጀምሯል።

የሶማሌ ክልል የጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዲ አዲል መሳሪያ ለማስፈታት  የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

በሁለቱም ወገኖች የክልል አመራሮች ዘንድ ችግሩን ለመፍታት ፍላጎት ቢኖርም እስካሁን መፍትሄ አልተገኝም ይላሉ።

የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቃቸውንም ለኢሳት ገልጸዋል።

የሞያሌው ግጭት ወደ ኬንያም ሊዛመት እንደሚችል የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ነው።

በአስርሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያውን በግጭቱ ምክንያት ተፈናቅለው ወደኬኒያ ድንበር መዝለቃቸውም ታውቋል።