በምዕራብ ጎንደር ዞን 8 ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 1/2011) በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን በኮኪትና ገንዳ ውሃ ከተሞች በመከላከያ ሰራዊት በተወሰደ ርምጃ 8 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።

ትላንት ገንዳውሃና ኮኪት በተባሉ አካባቢዎች ለተቃውሞ በወጡ ነዋሪዎችና በመከላከያ ሰራዊቱ መካከል በተፈጠረ ግጭት ስምንት ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።

የሱር ኮንስትራክሽን ተሽከርካሪዎች አካባቢውን ለቀው ሲወጡ በነዋሪው ተቃውሞ መቀስቀሱን ተከትሎ ነው ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ግጭቱ የተፈጠረው።

ህዝቡ መከላከያ ሰራዊቱ ከአካባቢው እንዲለቅ ጠይቋል።

የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ድርጅት ኤፈርት ንብረት የሆነው ሱር ኮንስትራክሽን በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች እያከናወነ ያለውን የፕሮጀክት ስራ በማቋረጥ ጓዙን ጥቅልሎ መውጣቱ ተቃውሞን ሲያስነሳ የመጀመሪያው አይደለም።

በርካታ የሱር ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች የጭልጋ ፕሮጀክትን ዘግተው ሊወጡ ሲሉ በባህርዳር መታገታቸው የሚታወስ ነው።

ሱር ኮንስትራክሽን በቅማንትና በአማራ ማህበረሰቦች መሀል በተፈጠረው ግጭት እጁ አለበት በሚል ተቃውሞ ይቀርብበታል።

የአማራ ክልልን ዘርፏል፣ ከወጣም ተፈትሾ የወሰደውን መልሶ መሆን አለበት የሚል ጥያቄ በህብረተሰቡ ዘንድ በስፋት እየተነሳ ነው።

በምዕራብ ጎንደር ገንዳውሃና ኮኪት ከተሞች ትላንት የተከሰተውና ለ8 ሰዎች ግድያ ምክንያት የሆነው ግጭትም ከዚሁ ከሱር ኮንስትራክሽን ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው የአካባቢው ነዋሪዎች የሚናገሩት።

ድርጅቱን በጥርጣሬ የሚመለከቱት ነዋሪዎች አካባቢውን ለቆ ለመውጣት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋል።

የሱር ኮንስትራክሽን እንቅስቃሴ የልማት አይደለም፣ መሳሪያ በድብቅ በማጓጓዝ በአካባቢው ሰላም እንዳይኖር አድርጓል የሚለው የነዋሪው ተቃውሞ ሲጠናከር ማሽነሪዎቹንና ተሽከርካሪዎቹን ጨምሮ ንብረቶቹን ይዞ እየለቀቀ ያለውን ድርጅት መንገድ ላይ በተቃውሞ በማስቆምና ተፈትሾ እንዲወጣ ጥያቄ ያቀረበው ህዝቡ የገጠመው ድርጅቱን ብቻ አልነበረም።

በመከላከያ ሰራዊት ከባድ መሳሪያ የታጀበው ሱር ኮንስትራክሽን እንጂ። ከዚያ በኋላ የሆነው ጥሩ አልነበረም።

ሱር ኮንስትራክሽንን አጅቦ ይጓዝ የነበረው መከላከያ ለተቃውሞ ወደ ወጣው ነዋሪ ላይ ተኩስ ከፈተ ይላሉ በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች።

ስምንት ሰዎች ተገደሉ። ከ20 በላይ ሰዎች ቆሰሉ። ከተገደሉት መካከል የ10 ዓመት ልጅ እንደሚገኝበት ነው ለማወቅ የተቻለው።

መከላከያ ሰራዊት መሳሪያ ባልያዘ ሰላማዊ ህዝብ ላይ የከፈተው ተኩስ ያደረሰው ጉዳት ይበልጥ ተቃውሞውን አጠናክሮታል።

ህዝቡ የሱር ንብረቶች ሳይፈተሹ እንዳይወጡ በሚለው አቋሙ በመጽናቱ ለጊዜው የተሽከርካሪዎቹ እንቅስቃሴ ተገቶ ውይይት መጀመሩ ተሰምቷል።

ኢሳት ጉዳዩን በተለመለከተ ወደ አማራ ክልል አስተዳደር ስልክ በመደውል መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ከአንድ ወር በፊት በቅማንትና በአማራ መካከል በተፈጠረው ግጭት በአካባቢው የሰፈረው የመከላከያ ሰራዊት አድሏዊ የሆነ ርምጃ መውሰዱን በተመለከተ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩ እንዲመረመር መወሰኑ የሚታወስ ነው።

የአማራ ክልል የደህንነትና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ብርጋዴ ጄኔራል አሳምነው ጽጌ በወቅቱ ለኢሳት በሰጡት ቃለመጠይቅ መከላከያ እንደተቋም ችግር የለበትም በግለሰብ ደረጃ የሚደረጉትን ግን እንዲጠየቁበት እናደርጋለን ማለታቸው ይታወሳል።