በምዕራብ ወለጋ እንዲሁም በምስራቅ ጉጂ የኦነግ ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት እርምጃ በመወሰድ ላይ ነው።

በምዕራብ ወለጋ እንዲሁም በምስራቅ ጉጂ የኦነግ ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት እርምጃ በመወሰድ ላይ ነው።
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ/ም ) የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት ካለፈው አርብ ጀምሮ በኦነግ ስም በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ላይ የመንግስት ወታደሮች በወሰዱት እርምጃ በብዙ ታጣቂዎች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ ደርሷል። የኦነግ ወታደሮችን ትጥቅ መፍታት የተቃወሙ ወጣቶች በየአካባቢው የተቃውሞ ሰልፎችን ሲያደርጉ ሰንብተዋል። በምዕራብ ወለጋ ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ውጥረቱ ዛሬም ድረስ መቀጠሉን ያነጋጋርናቸው የአይን እማኞች ገልጸዋል።
በምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ እና ዱጋ ዳዋ ወረዳዎች የኦነግ ደጋፊ ቄሮዎችና የመንግስት ወታደሮች የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውንና ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የኦነግ ሰራዊት ሙትና ቁስለኛ መሆናቸውን እንዲሁም ከመከላከያም የተጎዱ ወታደሮች እንዳሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ሁኔታው ያሳዘናቸው የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ የወጣቶች ድርጊት በጣም እንዳሳዘናቸው፣ ወጣቶቹ የመረጡት የትግል ስልት ስህተት መሆኑንና ጫካ የገቡ ወጣቶች እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የክልሉ ምክትል የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ እንደሚሉት ትጥቃቸውን ያልፈቱ የኦነግ ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት የተጀመረው እንቅስቃሴ መቀጠሉን ገልጸው፣ ከዚህ ውጭ ግን በክልሉ ከኦነግ ሰራዊት ጋር ጦርነት እየተካሄደ እንደሆነ የሚዘገበው ትክክል አይደለም ብለዋል።