በምዕራብ ኢትዮጵያ ግለሰቦችና የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 1/2011) የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት በምዕራብ ኢትዮጵያ ሕግና ስርአትን ለማስከበር በጀመረው ርምጃ 171 ግለሰቦች እንዲሁም የጦር መሳሪያዎችና ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ትጥቅ የማስፈታቱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ በምዕራብ ኢትዮጵያ ጦርነት ተከፍቶብኛል፣ሶስተኛ ወገን ባለበት እንደራደር በማለት መግለጫ ማውጣቱም አይዘነጋም።

የሃገር መከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሃመድ በሃገሪቱ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊቱ የሚመራ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን በገለጹ ማግስት ይፋ በሆነው ሪፖርት በቤንሻንጉል ጉምዝና ኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን 49 ክላሽንኮብ ጠመንጃ፣71 ሽጉጥ እንዲሁም ባህላዊ የጦር መሳሪያዎች መያዛቸው ተመልክቷል።

በሕገወጥነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ታጣቂዎች ከወሰዷቸው የመንግስት ንብረቶች 9 አምቡላንስ፣3 ቶዮታ ተሽከርካሪ እንዲሁም አንድ ከግለሰብ የተነጠቀን አንድ አይሱዙ ተሽከርካሪን ጨምሮ 14 ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተመልክቷል።

እንዲሁም 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ብርና ጥቂት የውጭ ሃገር ገንዘቦች ከታጣቂዎቹ ጋር መያዙንም ይፋ ከሆነው መንግስታዊ ሪፖርት መረዳት ተችሏል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በመከላከያው ስምሪት ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ መከላከያ ባደረገው የአንድ ሳምንት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።ይህው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመናገርም ጭምር።

በሁለትና ሶስት ሳምንት ግዜ ውስጥ ሁኔታዎች ወደ ነበሩበት እንደሚመለሱም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ሕዝቡ ነጻ አውጪዎች ናቸው ብሎ በሬ ያረደላቸው፣በኋላ እያስገደዱ በግና ዶሮ ጭምር እያሳረዱ ሕዝቡን ማሰቃየታቸውንም ገልጸዋል።

ታጣቂዎቹን ከሕዝብ እየነጠለ ትጥቅ እያስፈታ መቀጠሉንም አመልክተዋል።

ርምጃው እንደቀጠለ ባለበት በዚህ ወቅት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ በምዕራብ ኢትዮጵያ ጦርነት ተከፍቶብኛል፣ሶስተኛ ወገን ባለበት እንደራደር በማለት መግለጫ ማውጣቱ አይዘነጋም።