በመሬት መንሸራተት አደጋ የ8 ሰዎች ህይወት አለፈ

(ኢሳት ዲሲ–ነሀሴ 10/2010) በምስራቅ ጎጃም ዞን በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ የ8 ሰዎች ህይወት አለፈ።

በዞኑ ጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ስድስት የቤተሰብ አባላትና ሌሎች ሁለት ልጆች  ሞተዋል፡፡

የብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ ድርጅት በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች በክረምቱ ወራት የጎርፍ አደጋ እንደሚኖር አስቀድሞ ማስጠንቀቁም ታውቋል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን በእነገት ቀበሌ ልዩ ስሙ ወይን ውሃ በተባለ ጎጥ ነሀሴ 8/2010 ዓ.ም ከሌሊቱ 7 ሰዓት አካባቢ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት የ8 ሰዎች ህይወት ማለፉ ነው የተሰማው

በወይን ውሀ ጎጥ ከ17 በላይ መንደሮች የመሬት መንሸራት አደጋ ስጋት አሁንም አለባቸው።

ችግሩን ለመቅረፍ የተፈጥሮ ሀብት ስራ ቢሰራም ከአደጋው ሊታደጋቸው አልቻለም ነው የተባለው፡፡

ከአደጋው የተረፉ መንደሮች አሁንም በአስቸኳይ ካልተነሱ ተመሳሳይ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል ነው የተባለው፡፡

በአደጋው ቤት ከነሙሉ ንብረቱ በአካባቢው የተዘራ ሰብል ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በሙሉ ወድሟል፡፡

ቀሪ መንደሮችም በአደጋው ተጋላጭ በመሆናችን ወደሌላ አካባቢ እንድንዛወር መንግስት ሊረዳን ይገባል ብለዋል።

የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን  ለተጎጅ ቤተሰቦች ከቀበሌው ማህበረሰብና ከወረዳ ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረገ  ይገኛል፡፡

ተጋላጭ የሆኑ 17 የወይን ውሀ ጎጥ መንደሮችም  የወል መሬት ተሰጥቷቸው በሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ ለማድረግ  ከቀበሌው አመራር ጋር ስምምነት ላይ መደረሱ ታወቋል፡፡

የብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ ድርጅት በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች በክረምቱ ወራት የጎርፍ አደጋ እንደሚኖር ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።