በመላው የኦሮሚያ አካባቢዎች ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 5/2010)

የጨለንቆውን ጭፍጨፋ በመቃወም በመላው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ።

ተቃውሞው አዲስ አባባ ዙሪያ መድረሱንም ለማወቅ ተችሏል።

በወለጋ ጊምቢና ነጆ፣ በጂማ በአጋሮና በአብዛኛው የምስራቅ ሀረርጌ ከተሞች ተቃውሞ ሲካሄድ ውሏል።

በሞያሌ በአጋዚና በህዝቡ መሃል ግጭት ተፈጥሯል። በአምቦ የተገደሉ የአጋዚ ወታደሮች ቁጥር መጨመሩም እየተነገረ ነው።

ዛሬ በኦሮሚያ ክልል የተካሄዱትን ተቃውሞች በተመለከተ የተዘጋጀውን ዝርዝር ዜና ብሩታዊት ግርማይ ታቀርበዋለች

ባለፈው ሰኞ የህወሃት መከላከያ ሰራዊት በጨለንቆ ነዋሪዎች ላይ በወሰደው ርምጃ በትንሹ 20 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ በመላው ኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የተነሳው ቁጣ ሁለተኛና ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።

ማክሰኞ በዚያው በጨለንቆ፣ በደደር፣ በበዴሳ፣ በጭሮና በገለምሶ ህዝቡ ከያለበት ፈንቅሎ በመውጣት ለተገደሉት ሀዘኑን፣ ለገደሉት ደግሞ ቁጣውን አሳይቷል።

ዛሬም ተጨማሪ አካባቢዎች ተቀላቅለው የህወሃትን አገዛዝ ሲያወግዙ መዋላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በጂማ ይህው የህዝብ ቁጣ የተሰማ ሲሆን ነዋሪው አደባባይ በመውጣት የጨልንቆውን ጭፍጨፋ ያወገዘ ሲሆን የህወሀት መንግስት ከስልጣን እንዲወርድም ጠይቋል።

በአጋሮ ከተማም ተመሳሳይ የተቃውሞ ትዕይንት የተካሄደ ሲሆን የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከአጋዚ ወታደሮች ጋር ተፋጠው መዋላቸው ታውቋል።

በአጋሮ በተካሄደው ተቃውሞ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሚደረገው የጅምላ ግድያ ይቁም፣ የህወሃት ስርዓት በአስቸኳይ ከስልጣን ይውረድ የሚሉ መፈክሮች መሰማታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኦሮሚያው ተቃውሞ አዲስ አበባ ጫፍ የደረሰ ሲሆን በዙሪያው በሚገኙ ከተሞች ሲካሄድ መዋሉን ለማወቅ ተችሏል።

በፉሪ ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ በኦሮሞና አማራ ተማሪዎች ላይ አገዛዙ የሚፈጽመውን ግድያ እንዲያቆም ጠይቋል።

በዓለም ገና በህወሃት ደህንነቶች የተቀነባበረና በአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሙን የደረሰን መረጃ ላይ ተመልክቷል።

የታጠቁ ሃይሎች የአማራ ተወላጅ የሆኑ የዓለም ገና ነዋሪዎችን መኖሪያ ቤቶች እየመረጡ ድብደባ ሲፈጽሙ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

ይህ ተግባር በህወሀት በኩል ታቅዶ የሚካሄድ መሆኑን በመገንዘብ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም መልዕክት ተላልፏል።

በወለጋ በተለያዩ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ የተደረገ መሆኑ ሲታወቅ በተለይ በነጆና በጊምቢ ከፍተኛ የህዝብ ቁጣ የተስተናገደበት ትዕይንተ ህዝብ መደረጉን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በሁለቱ ከተሞች በተደረጉት የተቃውሞ ሰልፎች የጨለንቆው ጭፍጨፋ የተወገዘ ሲሆን ገዳዮች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ተጠይቋል።

በሞያሌ ከተማ ዛሬ በአጋዚ ወታደሮችና በህዝቡ መካከል ግጭት የተፈጠረ ሲሆን በተለይ የከተማዋ ወጣቶች በአጋዚ ሰራዊት ላይ ድንጋይ በመወርወር ተቃውሞ መግለጻቸው ታውቋል።

በሌላ በኩል ከትላንት በስትያ በኦሮሚያ ፖሊስና በአጋዚ ሰራዊት መሀል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የተገደሉት የአጋዚ ወታደሮች ቁጥር ከሁለት በላይ መሆኑ እየተገለጸ ነው።

በዕለቱ ሁለት የአጋዚ ወታደሮች ብቻ ተገድለዋል የተባለ ሲሆን ቁጥሩ ከዚያም የሚበልጥ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።