በሕገወጥ መንገድ የገቡ የጦር መሳሪያዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 28/2011)ወደ ኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ በሶስት ወራት ውስጥ የገቡ የጦር መሳሪያዎች ብዛት ከ1 ሺ 500 በላይ መብለጡን ፖሊስ ገለጸ።

የጦር መሳሪያዎቹም በአብዛኛው ቱርክ ሰራሾች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በብዛት የሚገባውም በሱዳን በኩል እንደሆነ ተመልክቷል።

በፌደራል ፖሊስ የተደራጁ ልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር ከተማ ደባልቄ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት እስከ መስከረም መጨረሻ ባሉት ሶስት ወራት 1 ሺ 560 ሕገ ወጥ ሽጉጦች ወደ ሃገር ቤት ገብተው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

5 መትረየስና 5 ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎችም በተመሳሳይ በሕገወጥ መንገድ ወደ ሐገር ውስጥ መግባታቸውንም ገልጸዋል።

የጦር መሳሪያዎቹ በአብዛኛው የቱርክ ስሪት መሆናቸውን የገለጹት ኮማንደር ከተማ ደባልቄ በሱዳን ድንበር በኩል አልፎ በብዛት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ላይ መሆኑንም አመልክተዋል።

በጉዳዩ ላይ አዲስ አበባ ከሚገኘው የቱርክ ኤምባሲ ጋር መነጋገራቸውንም ለመገናኛ ብዙሃነስረድተዋል።

በሕገወጥ መንገድ የገቡት የተጠቀሱ ብቻ ሳይሆኑ የተያዙና ያለፉ መኖራቸውንም አመልክተዋል።

ሳይያዙ ያለፉ መኖራቸው የተደረሰበትም በግዢና ሽያጭ ሒደት ውስጥ እንደሆነም ተናግረዋል።

በሕገወጥ ጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች ላይ የሚጣለው ቅጣት ማነሱ ለችግሩ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ተናግረዋል።

የጦር መሳሪያ ማዘዋወራቸው የተረጋገጠባቸው ሰዎች ፍርዳቸው ሶስት ወር መሆኑንና ዋስትናም በሕጉ ስለማይከለከል ወንጀለኞቹ ተመልሰው በቀደመው ወንጀል እንዲቀጥሉ ያደርጋቸዋል ብለዋል።