በሌብነት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን የማሰሩ ተግባር መቀጠሉ ታወቀ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 5/2009) በሌብነት የተጠረጠሩ የ210 ግለሰቦች ሀብትና ንብረት በታገደ ማግስት ተጨማሪ ተጠርጠሪዎችን የማሰሩ ርምጃ መቀጠሉ ታወቀ።
መንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን ጠቅላይ አቃቢ ህግን ጠቅሰው እንደዘገቡት የመንገዶች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በዚህም በሌብነት ተጠርጥረው ወደ ወህኒ የወረዱ ታሳሪዎች ቁጥር 55 ደርሷል።
የመንገዶች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ መታሰራቸውን ተከትሎ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የታሰሩትን ሃላፊዎች ቁጥር ወደ 9 ከፍ አድርጎታል።
የቀድሞው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል እንዲሁም ሁለት ምክትሎቻቸው አቶ በቀለ ንጉሴና አቶ አብዲ መሀመድን ጨምሮ 8 ተጠርጠሪዎች ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስቀድሞ መታሰራቸው ይታወሳል።
የትላንቱን ጨምሮም በሌብነት ተጠርጥረው ወደ ወህኒ የወረዱ ታሳሪዎች ቁጥር 55 መድረሱን መረጃዎች አመልክተዋል።
በተያያዘ ዜና ሐሙስ ነሐሴ 4/2009 ሐብትና ንብረታቸው ከታገደው 210 ግለሰቦች ውስጥ የአሰር ኮንስትራክሽን ባለቤቶች አስቀድሞ በደረሳቸው መረጃ ከሀገር መውጣታቸው ታውቋል።
የዶክተር አርከበ እቁባይ ቤተሰብ ንብረት የሆነው አሰር ኮንስትራክሽን ባላቤቶች የማነ አብርሃና ሚካኤል አብርሃ እስራቱ ሳይጀመር ወደ አሜሪካ መሸሻቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።