በሊቢያ ኢትዮጵያውያን በስቃይ ላይ ናቸው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 28/2011) በሊቢያ ኢትዮጵያውያን በስቃይ ላይ መሆናቸው ተገለጸ።

በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ ከ20 በላይ ኢትዮጵያውያን ለቀናት ምግብና ውሃ አጥተው በከፍተኛ አደጋ ውስጥ እንደሚገኙ ኢሳት ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።

አብዛኞቹ ከጎንደር የተሰደዱ መሆናቸውን የሚገልጹት ኢትዮጵያውያኑ ባለፈው ቅዳሜ ገጀራና የጦር መሳሪያ የያዙ የሊቢያ ታጣቂዎች ድብደባ ፈጽመውባቸው ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

ከእነዚህ ኢትዮጵያውያን መካከል የአምስት ቀን አራስ እናት እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል።

ከኢትዮጵያውያኑ መካከል 10 ኢትዮጵያውያን ታፍነው መወሰዳቸውም ታውቋል።ከነዚህም 6ቱ ወንዶች ሲሆኑ 4ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው ተብሏ።

ኢትዮጵያውያኑ በረሃብና በድብደባ ህይወታችን ከማለፉ በፊት ወገን ይድረስልን ሲሉ ጥሪ አድርገዋል።