በሃረሪ ክልል የሚገኙ የኦሮሞ የአገር ሽማግሌዎች መብታችን ካልተከበረልን ወደ ኦሮምያ እንጠቃለል አሉ

ግንቦት ፰ ( ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሃረሪ ክልል በገጠር አካባቢ የሚኖሩ የኦሮሞ አገር ሽማግሌዎች ለኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንት በጻፉት የአቤቱታ ድብዳቤ በሃረሪ ክልል ውስጥ የኦሮሞ ተወላጆች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም፣ ከፖለቲካና ከኢኮኖሚ ጉዳዮች ውጭ በመሆናችን አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ ወደ ኦሮምያ ክልል እንድንጠቃለል እንጠይቃለን ብለዋል።
ከ99 በመቶ በላይ የሚሆኑ በክልሉ የሚገኙ የንግድ ቤቶች እና ቦታዎች የተያዙት በሃረሪ ብሄራዊ ሊግ ባለስልጣናትና ዘመዶቻቸው ነው የሚሉት የአገር ሽማግሌዎች፣ የክልሉ የኦህዴድ ባለስልጣናትም በጥቅም ተይዘው መብታችንን ሊያስከብሩልን አልቻሉም ሲሉ ጠቅሰዋል።
በሃረር እስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር የያዙት የአማራ፣ የኦሮሞና የጉራጌ ተወላጆች ናቸው የሚሉት የአገር ሽማግሌዎች፣ እንዲህ አይነቱ ኢ ፍትሃዊ አሰራር እንዲቆምም ጠይቀዋል። የስልጣን እና የኢኮኖሚ ክፍፍሉ ፍትሃዊ ይሁን የሚሉት የአገር ሽማግሌዎች ፣ ይህ ካልሆነ ግን በአስቸኳይ አካባቢው ወደ ኦሮምያ ይጠቃለል ብለዋል። የአገር ሽምግሌዎችን ጥያቄ ተከትሎ ክልሉ ሰሞኑን ቦታ የምትፈልጉ ተመዝገቡ የሚል ማስታወቂያ ማውጣቱን የክልሉ ወኪላችን ገልጿል።
በሃረሪ ክልል የሚገኙ የኦሮሞ፣ የአማራና የጉራጌ ተወላጆች ክልሉን በሚመራው በአናሳው የሃረሪ ብሄራዊ ሊግ የዘር መድሎ እንደሚደርስባቸው በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።