በሁለት የቱርክ ባለሃብቶች የተቋቋመ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ለጨረታ ሽያጭ ቀረበ

ኢሳት (ጥር 2 ፥ 2009)

ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ አንድ ቢሊዮን ብር አካባቢ ብድር በመውሰድ በሁለት የቱርክ ባለሃብቶች የተቋቋመ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ባለሃብቶቹ ከሃገር በመኮብለላቸው ምክንያት ፋብሪካው ለጨረታ ሽያጭ ቀረበ።

በሁለት ባለሃብቶች ከአምስት አመት በፊት የተቋቋመው ኤል ሲ አዲስ (L. C. Addis) የተሰኘው ይኸው የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ግንባታን ለማከናወንና ማሽኖችን ለመግዛት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ወደ 900 ሚሊዮን ብር አካባቢ በብድር መውሰዱ ታውቋል።

የፋብሪካው ባለሃብቶች መጥፋት ተከትሎ ለዚሁ ተቋም የጥጥ ምርት ሲያቀርቡ የነበሩ 11 ጥጥ አቅራቢ ባለሃብቶች ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ እንዳልተከፈላቸው ለመንግስት አስታውቀዋል።

ፋብሪካውን የተረከበው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በአጠቃላይ ለድርጁቱ የተሰጡ 933 ሚሊዮን ብር እዳን ለማስመለስ ፋብሪካውን በጨረታ ለመሸት መወሰኑን የልማት ባንክ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሃይሉ ምስጋናው ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ባለፈው ወር በተመሳሳይ ሁኔታ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሰበታ ከተማ የሚገኝ አንድ የቱርክ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካን ለጨረታ አቅርቦ ገዢ ማጣቱ መዘገቡ ይታወሳል።

ሳይጊን ዲማ የተሰኘው ይኸው ፋብሪካ ከንግድ ባንክ ወደ 600 ሚሊዮን ብር አካባቢ ብድርን ወስዶ የነበረ ሲሆን፣ ከመንግስት ጋር በሽርክና ሲሰራ የቆየው ስራ ትርፋማ ባለመሆኑ ምክንያት በሁለቱ ወገኖች የተደረሰ ስምምነት ፈርሶ ፋብሪካው ለጨረታ እንዲቀርብ መደረጉ ታውቋል።

ይሁንና የብሄራዊ ንግድ ባንክ ፋብሪካውን በጨረታ ለመሸጥ ለስድስት ወራቶች ተደጋጋሚ ጥረትን ቢያደርግም ተዢ አለማግኘቱን ለመረዳት ተችሏል።

ልዩ የማበረታቸው ጥቅማጥቅም ተደርጎላቸው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የቱርክ የጨርቃ – ጨርቅ የውጭ ንግድ ገቢ በ21 በመቶ አካባቢ ማሽቆልቆሉንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

መንግስት ለጨረታ አቅርቧቸው ያሉትን ሁለት ግዙፍ የቱርክ ፋብሪካዎች ለማስተዳደር ተጨማሪ ገንዘብ እያወጣ መሆኑም ይነገራል።

ከ1ሺ በላይ ሰራተኞች ያሉትን የኤል ሲ አዲስ (L. C. Addis) ፋብሪካ ገዢ እስኪያገኝ ድረስ በመንግስት የደሞዝ ክፍያን ጨምሮ የተለያዩ ወጪዎችን እየሸፈነ እንደሚቆይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሃላፊዎች አስረድተዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በጋምቤላ ክልል ከመንግስት ብድር የወሰዱ ባለሃብቶች የወሰዱትን ብድር ሳይከፍሉ ከሃገር መኮብለላቸው ይታወሳል።