ቅማንትን በአዲስ አስተዳደር ለመከለል የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ የፌደሬሽን ምክር ቤት ማጽደቁ ተሰማ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 1/2010) በህወሀትና ብአዴን የተዘጋጀውንና ቅማንትን በአዲስ አስተዳደር ለመከለል የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ የፌደሬሽን ምክር ቤት ማጽደቁ ተሰማ።

ያለህዝበ ውሳኔ በህወሀት ቀድመው የተካለሉት የ42 ቀበሌዎች ጉዳይ አሁንም የህዝብ ጥያቄ ማስነሳቱ ታውቋል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ያጸደቀበት ምክንያት ያለህዝብ ፍቃድ የተካለሉትን 42 ቀበሌዎች ህጋዊ ሽፋን ለመስጠት ነው ሲሉ ታዛቢዎች ይገልጻሉ።

የጎንደርን ህዝብ ለመከፋፈል የሚደረገውን የስርዓቱን ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ ህዝቡ በንቃት እየተከታተለ እንዲታገለው የጎንደር ህብረት ጥሪ አድርጓል።

መስከረም 7/2010 ህወሃት የፈለገውና የፈቀደው ሕዝበ ውሳኔ ሲካሄድ ውጤቱ ቀድሞም ይታወቅ ነበር።

ለዘመናት ሳይለያዩ የኖሩትን የጎንደርና የቅማንት ማህበረሰብ በአስተዳደር ወሰን ለይቶ ለማካለል በሚል የልዩነት ምርጫ ይዞ የመጣው የህወሃት መንግስት ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ አድርጓል።

በ12 ቀበሌዎች ታስቦ የነበረው ይህው ህዝበ ውሳኔ 4ቱ ቀበሌዎች በእኛ ምርጫ ሊደረግ አይገባም በማለታቸው በ8ቱ ብቻ እንዲደረግ ተወሰነ።–ህዝበ ውሳኔውም ተካሄደ።

ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑትና በ7 ቀበሌዎች የሚገኙት መራጮች በነበረው አስተዳደር ስር መቆየትን ሲመርጡ አንድ ቀበሌ ግን በህወሃት እንዲካለል በተፈለገው የቅማንት አስተዳደር ስር መሆንን መረጠ።

ሆኖም በዚህም ቀበሌ የነበረው ድምጽ በህወሃት ሰርጎ ገብ ካድሬዎች በመጭበርበሩ መሆኑ ተጠቅሶ ተቃውሞ ቀርቦበታል።

እስካሁንም የቀበሌዋ ነዋሪዎች ድምጻችን አልተከበረም የሚል ተቃውሞ እያሰሙ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

ሆነም ቀረም የ8ቱ ቀበሌዎች ውጤት በምርጫ ቦርድ አማካኝነት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መላኩ ተገለጸ።

ዛሬ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝበ ውሳኔውን ውጤት ማጽደቁን አስታዉቋል።

በዚህም መሰረት ሰባቱ ቀበሌዎች በነበረው አስተዳደር ስር ለመቆየት መወሰናቸውን ተቀብሎታል።

አንደኛው ቀበሌ በአዲሱ የቅማንት አስተዳደር ስር እንዲሆን በውጤቱ መሰረት ማጽደቁንም ገልጿል።

የጎንደር ህብረት አመራር አቶ አበበ ንጋቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱን የዛሬ ውሳኔ ብዙም ቦታ የሚሰጠው አይደለም ይላሉ።

ቀድሞውኑ ማህበረሰቡ የማይቀበለው ነበር።ያንንም ነው በሕዝበ ውሳኔው ያረገገጠው ብለዋል አቶ አበበ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የግጨውን ህዝበ ውሳኔ ውጤት ከ10 አመታት በላይ በመዝገብ ቤት ውስጥ ቆልፎበት ከቆየ በኋላ በዚህ አመት መግቢያ ላይ ህወሃት የአቶ ገዱ አንዳርጋቸውን እጅ በመጠምዘዝ ግጨውን መውሰዱ የሚታወስ ነው።

ባለፈው መስከረም 7 የተደረገው ህዝበ ውሳኔ ውጤት የግጨው እጣ ፈንታ እንዳይገጥመው የሰጉ ወገኖች ቢኖሩም ፌዴሬሽን ምክር ቤት ውጤቱን ሊያጸድቀው ችሏል።

አቶ አበበ ንጋቱም ሆኑ አንዳንድ የአካባቢውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ወገኖች የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ በ42 ቀበሌዎች የተነሳውን የህዝብ ጥያቄ ለማድበስበስ ታልሞ የተደረገ ነው።

ያለህዝብ ፈቃድ 42 ቀበሌዎች በቅማንት አስተዳደር ስር እንዲሆኑ ህወሃት ቀደም ብሎ ውሳኔ ላይ የደረሰ ሲሆን ህዝቡ ድምጹን እንዳይሰጥ መገደቡ ታውቋል።