ሰራዊቱ ያሉበትን ችግሮች ለመቅረፍ የማሻሻያ ርምጃዎች በመውሰድ ላይ ናቸው

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 5/2011)የኢትዮጵያ ሰራዊት ያሉበትን ችግሮች ለመቅረፍ በየደረጃው የማሻሻያ ርምጃዎች በመውሰድ ላይ መሆናቸውን ጄኔራል ሰአረ መኮንን ገለጹ።

ወደ ቤተመንግስት የተጓዙትን የሰራዊቱን አባላት ድርጊት ጋጠወትና ጸረ ሕገ መንግስት በማለት የጠቀሱት ጄኔራል ሰአረ መኮንን ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ አመራሮቹ መታሰራቸውን ገልጸዋል።

አስተማሪ የሆነ ርምጃ እንደሚወስድም ቃል ገብተዋል።

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ መስከረም 30/2011 ወደ ቤተመንግስት የተንቀሳቀሱት የአጋዚ ክፍለ ጦር አባላት መሆናቸውን የገለጹት ጄኔራል ሰአረ መኮንን ይህው ሃይል በሶማሌ ክልል የተፈጠረውን ችግር ለማረጋጋት እዚያው መቆየቱን አስታውሰዋል።

አዲስ አበባና አካባቢዋ ከተፈጠረው አለመረጋጋት ጋርም በተያያዘ ይህው ሰራዊት ግዳጅ ውስጥ መቆየቱን የገለጹት ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጄኔራል ሰአረ መኮንን ያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሆኖም ጥያቄውን ለማቅረብ የሔደበት መንገድ ግን ጸረ ሕገ መንግስትና ጋጠወጥነት ነው ሲሉ ትችተዋል።

የሰራዊቱ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሁም ለሁለት ቀናት ደግሞ ከሰራዊቱ አመራሮች ጋር መወያየታቸውንና ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

በድርጊታቸውም መጸጸታቸውን አመልክተዋል።

የሰራዊቱ አባላት የዲሲፒሊን ችግር መፈጸማቸውን ቢገልጹም ድርጊቱ ከዲሲፒሊን ያለፈ ጸረ ህገ መንግስት ነው ያሉት ጄኔራል ሰአረ መኮንን አመራሮቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክተዋል።

ከግለሰቦቹ ጀርባ ማን አለ የሚለው በቀጣይ ይመረመራል ያሉት ጄኔራል ሰአረ መኮንን አስተማሪ የሆነ ርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል።

የሰራዊቱን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በካምፕ ውስጥ ለቀለብ ይመደብላቸው የነበረው 650 ብር ወደ 850 ከፍ መደረጉን የገለጹት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ሰራዊቱ በራሱ ወጪ ዩኒፎርም እንዲገዛ የተጣለበት ግዳጅ መነሳቱና መንግስትም በራሱ ዩኒፎርም እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል።