ሩስያ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ታላቅ የተባለ የጦር ልምምድ ማድረግ ጀመረች

ሩስያ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ታላቅ የተባለ የጦር ልምምድ ማድረግ ጀመረች
( ኢሳት ዜና መስከረም 01 ቀን 2011 ዓ/ም ) 300 ሺ የሚጠጉ የሩስያ ወታደሮች በምስራቅ ሳይቤሪያ በጀመሩት ወታደራዊ ልምምድ፣ 3200 ወታደሮችን የላከቸው ቻይናና ሞንጎልያም ተካፍለዋል።
ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በሁዋላ በአይነቱ ልዩ ነው የተባለው ፣ ቮስቶክ 2018 የተባለ ስያሜ የተሰጠው ወታደራዊ ልምምድ አላማው የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን አገሮች ወይም ኔቶ በሩስያ ላይ የሚያሳድረውን ተጽኖ ለመቋቋም ተብሎ መዘጋጀቱ ተነግሯል።
በልምምዱ ላይ የሩስያ ጦር 36 ሺ ታንኮች እና ከ1000 ያላነሱ የጦር አውሮፕላኖች ተሳታፊ ይሆናሉ። የቻይና ጦር ከሩስያ ጋር አብሮ ልምምድ ማድረጉ ጉዳዩን በስጋት ለሚመለከቱት የምዕራብ አገራት መልካም ዜና አይደለም። በአለም አቀፍ ግንኙነታ ሰላማዊነት የምትሰብከው ቻይና፣ ሞስኮን ተጠቅማ በወታደራዊም መስክ በአለም ሃያል ሆና ለመውጣት ያላትን ፍላጎት እንደሚያሳይ ምሁራን ይናገራሉ።
ሁለተኛው የአለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በሁዋላ በሩስያና በምዕራብ አገራት መካከል የነበረው መልካም ግንኑነት ሩስያ በዩክሬን ጣልቃ ከገባችና ክሪሚያን ከያዘች በሁዋላ እየተባለሸ መጥቷል።