ሜቴክ እንደገና ሊደራጅ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 6/2011) የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ወታደራዊ ምርት የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ለመከላከያ ሚኒስቴር በማስረከብ የብሄራዊ የኢንዱስትሪያል ምህንድስና ኮርፖሬሽን በሚል ስያሜ እንደገና ሊደራጅ ነው።

የኮርፖሬሽኑ የኮሜርሻልና ሲቪል ምርቶች ኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልዓዚዝ መሀመድ እንደገለጹት ሜቴክ አዲሱን ስያሜ ይዞ የሲቪልና የንግድ ምርቶችን ብቻ የሚያመርት ይሆናል።

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከብቃት እጦትና ከብክነት ጋር በተያያዘ ስሙ በተደጋግሚ ሲነሳ ቆይቷል።

እጁ ላይ የነበሩ በርካታ የስኳር ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ አቅቶት እሰከመቀማትም ደርሷል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሃይድሮ መካኒካል ስራዎችን ወስዶ መስራት ባለመቻሉም ቢሊየን ብሮች እንደባከነ ተሰምቷል።

ሜቴክ ችግር  ካለበት ተጠያቂው እኔ ነኝ በማለት በፓርላማ ቀርበው ሃላፊነቱን እወስዳለሁ ያሉት የቀድሞው የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጂኔራል ክንፈ ዳኜ ከስልጣናቸው ቢለቁም እስካሁን ተጠያቂ አልተደረጉም።

እናም በአዲሱ አድረጃጀት መሰረት  በሜቴክ ስር የንበሩና ወታደራዊ ምርቶችን ሲያመርቱ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ለመከላከያ ሚኒስቴር እንዲሰጡ ተደርገዋል ተብሏል።

በዚህ መሰረት ሜቴክ አዲሱን ስያሜ ይዞ የሲቪልና የንግድ ምርቶችን ብቻ የሚያመርት ሲሆን፥ የብሄራዊ የኢንዱስትሪያል ምህንድስና ኮርፖሬሽን የሚል አዲስ ስያሜ ሊሰጠው እንደታሰበም ተናግረዋል።

ለዚህ አዲስ አደረጃጀትም ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ነው የተነገረው።

የኮርፖሬሽኑ የኮመርሻልና ሲቪል ምርቶች ኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልዓዚዝ መሀመድ እንደገለጹት ሜቴክ እስካሁን 14 ኢንዱስትሪዎችን ሲያስተዳድር ቆይቷል።

ከነዚሁ መካከልም ሜቴክ ሙሉ ለሙሉ ወታደራዊ ምርቶችን የሚያመርቱ አራት ኢንዱስትሪዎችን ለመከላከያ ሚኒስቴር እንዲያስረክብ በመንግስት ተወስኗል ነው ያሉት።—– ሆሚቾ ኢንዱስትሪ፣ ደጀን አቪየሽን፣ ጋፋት አርማመንት እና ልዩ ትጥቆች አምራች ኢንዱስትሪ የተባሉትን ድርጅቶች።

ቀሪ ዘጠኝ ኢንዱስትሪዎች በሜቴክ ወይም ወደፊት የብሄራዊ ኢንዱስትሪያል ምህንድስና ኮርፖሬሽን የሚል ስያሜ በሚሰጠው ተቋም ውስጥ የሚተዳደሩ ይሆናል ብለዋል።

ቢሸፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ወታደራዊም ሆነ የሲቪል ምርቶችንም ስለሚያመርት በማን እጅ መሆን ይኖርበታል የሚለውን ጉዳይ ለማጥናት ኮሚቴ መቋቋሙን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።