ሜቴክ ለመለስ ዜናዊ ልጅ የ56ሺህ 205 ዶላር ክፍያ ፈጽሟል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 21/2011)የሜቴክ ዋና ሃላፊ ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ልጅ የ56ሺህ 205 ዶላር ክፍያ በመፈጸማቸው ተጨማሪ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ለማይታወቅ ተቋም የ4 ሚሊየን ዶላር ክፍያ በመፈጸም የሃሰት ዲግሪዎችን ሲገዙ መቆየታቸውም ተጋልጧል።

የቀድሞው ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሁለተኛ ልጅ ለሆነችው ማርዳ መለስ በሁለት ዙር የ56 ሺህ 205 የአሜሪካን ዶላር ከሜቴክ እንዲከፈል በማድረጋቸው ተጨማሪ የሌብነት ወንጀል ክስ የቀረበባቸው ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ልጅ ከሜቴክ ያወጡት ገንዘብ በኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር 1 ሚሊየን 250 ሺህ 886 ብር እንደሆነም ተገልጿል።

ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ለማርዳ መለስ ገንዘቡን የከፈለበት ምክንያት በግልጽ አልተመለከተም ሆኖም የአቶ መለስ ልጅ በውጭ ሃገር እየከፈለች በመማር ላይ መሆኗ ሲገለጽ ቆይቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በሜቴክ በህገ-ወጥ መንገድ የባከነውንና የተቋሙ ሃላፊዎች ከሌላ ግለሰብ ጋር በመሆን የዘረፉትን 4 ሚሊየን ዶላር በተመለከተም አቃቤ ህግ አስታውቋል።

የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ላላስተማራቸው የትምህርት ዓይነቶችና ባልተቀረጸ ካሪኩለም ለተማሪዎች የማስተርስና የዶክተሬት ዲግሪ እንዲሰጥ ከአንድ ግለሰብ ጋር በፈጠሩት ሽርክና የባከነውን የሃገር ሐብት በተመለከተ አቃቤ-ህግ በፍርድ ቤት ያቀረበውን መረጃ ሪፖርተር ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል።

በዚህም ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና ግብረ አበሮቻቸው ዶክተር መኮንን ገብረ ሚካኤል ከተባለ ግለሰብ ጋር በመመሳጠር 3 ሚሊየን 901 ሺህ 140 የአሜሪካን ዶላር የሃገር ሃብት ማባከናቸው ተመልክቷል።

ዶክተር መኮንን ገብረ ሚካኤል የተባሉት ግለሰብ የተለያዩ የውጭ ሃገር ዜጎችን በቱሪስት ቪዛ ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ ካደረጉ በኋላ ከሜቴክ ሰዎች ጋር በመመሳጠር ክፍያውን በውጭ ምንዛሪ መቀበላቸው ይፋ ሆኗል።

ከኢትዮጵያ መንግስት ሃብት 3 ሚሊየን 901 ሺህ 140 የአሜሪካን ዶላር ቢፈጸምም በምላሹ የተገኘ ትምህርትም ሆነ ሌላ ነገር አለመኖሩ ተገልጿል።

ሆኖም ላልተማሩ ሰዎች በማያውቁት ዘርፍ የማስተርስና የዶክተሬት ዲግሪ እንደተሰጣቸው ተገልጿል።