ማንነትን ማክበርና ማስከበር የልዩነት ግንብን መገንባት አይደለም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ /2011) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ማንነትን ማክበርና ማስከበር አጥር ማጠርና የልዩነት ግንብ መገንባት አይደለም ሲሉ ገለጹ።

በጎንደር በተካሄደውና በአማራና ቅማንት ማህበረሰብ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሚመክረው መድረክ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት መሪዎች ከማለፋቸው በፊትየማያልፍ  ጠባሳ ለትወልዱ ጥለው እንዳያልፉ ሊጠነቀቁ ይገባል።

አቶ ደመቀ መኮንን እንዳሉት ማንነትን ማክበርና ማስከበር አጥር ማጠርና የልዩነት ግንብ መገንባት አይደለም ።

ህዝብን ማድመጥና ታሪካዊ ወሰኑን ማስከበር እንጅ ያደረ ጥያቄ ነው እያሉ ማለፍ ታሪኩ ያለፈበት ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።

እናም የምናልፍ መሪዎች የማያልፍ ጠባሳ ጥለን እንዳናልፍ ልንጠነቀቅ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ድርጅትና መሪዎች ያልፋሉ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ህዝብና ታሪክ ቀጣይነት አላቸው ብለዋል።

ግጭት ለታላቅ ሀገርና ተስፋ ለሰነቀ ህዝብ የሚመጥን እንዳልሆነም በንግግራቸው አንስተዋል።

ሃገራችን ያከበረችንን ያክል አላከበርናትም ያሉት አቶ ደመቀ የሃገር ግንባታ ጊዜ ይወስዳልና በትዕግስት ሀገር ልንገነባ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ህዝቡ አብሮ መኖሩንና መዋለዱን እንዲሁም በደም መተሳሰሩን አውስተዋል።

በአማራ ክልል ሰሜን እና ማእከላዊ ጎንደር የቅማንትን የማንነት ጥያቄ ሰበብ በማድረግ በተፈጠረ ግጭት ሰሞኑን ከ 54 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

የክልሉ የሰላምና ደሕንነት ቢሮ ሃላፊ ብርጋዴር ጂኔራል አሳምነው ጽጌ የግጭቱ መንስኤዎች ሕወሃቶች ናቸው ማለታቸውም አይዘነጋም ።

በጎንደር ከተማ ዛሬ በተጀመረው የአማራና ቅማንት ማህበረሰብ የምክክር መድረክ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ  ከፌዴራልና ከክልል የተውጣጡ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ከማዕከላዊ፣ ምዕራብና ሰሜን ጎንደር የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች በውይይት መድረኩ እየተሳተፉ ይገኛል።