መከላከያን ጥለው የሚጠፉ ወታደሮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል

ግንቦት ፰ ( ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የመከላከያ ምንጮች እንደገለጹት በቅርቡ በአማራና በኦሮምያ አካባቢዎች የተነሱትን ህዝባዊ ተቃውሞዎች ተከትሎ፣ ስርዓቱን በተለያየ መንገድ አናገለግልም በማለት እየጠፉ የሚሄዱ ወታደሮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ ገዢው ፓርቲ አዳዲስ ወታደሮችን በፍጥነት ለመመልመልና በተለያዩ መንገድ ከመከላከያ የተሰናበቱትን ተመልሰው እንዲገቡ ጥሪ ለማድረግ ተገዷል።
ባለፉት 4 ወራት በርካታ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች መጥፋታቸው ለመከላከያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ ጠፍተው የሄዱ ወታደሮች እየታደኑ እንዲያዙ የሚል ውሳኔ ተላልፏል። ወታደሮቹ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስከሚነሳበት ጊዜ ድረስ ምንም አይነት የመልቀቂያ ጥያቄ እንዳያቀረቡ መታዘዛቸው በወታደሮች ላይ ተስፋ መቁረጥን ማስከተሉ ፣ ተተኪ ሃይል ሊገኝ ባለመቻሉ በግዳጅ ላይ ባሉ ወታደሮች ላይ ያለው የስራ ጫና መጨመር እንዲሁም የኑሮ ሁኔታው መበላሸት ሰራዊቱን እየለቀቁ ለሚሄዱ ወታደሮች ዋና ምክንያት እንደሆነ በሪፖርቱ ተመልክቷል።
ኢሳት ያነጋገራቸው ወታደሮች እንደሚገልጹት ግን የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተለይ በአማራና በኦሮምያ አካባቢ ያአጋዚ ወታደሮች ያደረሱትን ጨፍጨፋ የተቃወሙ በርካታ የሰራዊት አባላት ከእንግዲህ ይህን ስርዓት አናገለግልም በማለት መልቀቃቸውን ተናግረዋል። ሰራዊቱን ከለቀቁ መካከል በአጋዚ ውስጥ በሃላፊነት ሲሰሩ የነበሩ ሰዎችም ይገኙበታል። በሰራዊቱ ውስጥ ያለው የብሄር ልዩነት የፈጠረው ተጽኖም እየለቀቁ በሚጠፉ ወታደሮችም ላይ በግልጽ እንደሚታይ ምንጮች ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተለያዩ አካባቢዎች የተለጠፉ አዲስ የቅጥር ማስታወቂያዎችም የሚፈለገውን ውጤት አላመጡም። በተለይ በኦሮምያ፣ በአማራ፣ ሀረሪና ደቡብ አካባቢዎች በክልል ደረጃ የሚመዘገቡ አዲስ ምልምል ወታደሮች እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል።
ገዢው ፓርቲ በተለያዩ ምክንያቶች ከሰራዊቱ ለተመለሱ የቀድሞ ወታደሮች ጥሪ ያደረገ ሲሆን፣ ወታደሮቹ ወደ በተመድ በኩል ወደ ሱዳን በሰላም አስከባሪነት እንደሚዘምቱ እንዲሁም ቤት እና ከፍተኛ ክፍያ እንደሚሰጣቸው እየተናገራቸው ቢሆንም፣ በዚህም በኩል የተመዘገቡ ተመላሽ ወታደሮች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነው።
በየዞኑ የሚገኙ አርሶአደሮችን ጠመንጃ እንሰጣችሁዋለን በማለት እና በማስፈራራት በያካባቢያቸው ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ ከተደረገ በሁዋላ፣ በሂደት ወደ እግረኛ ወታደርነት ለመቀየር መታሰቡንም ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
በሰሜን ጎንደር ሲካሄድ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ በህዝብ ላይ እንዲተኩሱ ታዘው አንተኩስም ያሉ በርካታ ወታደሮች ታፍነው መታሰራቸውንም ምንጮች አክለው ገልጸዋል። የእነዚህ ሰዎች እጣ ፋንታ ምን እንደሆነ እስካሁን አለመታወቁንም አክለው ገልጸዋል። ኢሳት ሁኔታዎች እንደተመቻቹለት ከአጋዚ ሰራዊት የጠፉ ወታደሮችን አቅርቦ የሚያናግር መሆኑን ለመገለጽ ይወዳል።