መንግስት ከ70 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ ስኳርን ከህንድ ማስገባት ጀመረ

ኢሳት (ሰኔ 28 ፥ 2008)

ለሃገር ውስጥና ለአለም አቀፍ ገበያ ስኳርን ያቀርባሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩ የስኳር ፋብሪካዎች ወደስራ አለመባታቸውን ተከትሎ መንግስት ከ70 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ ስኳርን ከህንድ ማስገባት ጀመረ።

አራት የስኳር ኮርፖሬሽኖች ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ተመድቦላቸው ከሶስት አመት በፊት ስራ ይጀምራሉ ቢባሉም ፋብሪካዎቹ ግንባታቸው ገና አለመጠናቀቁ ታውቋል።

ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውና ስራቸው በመስተጓጎሉ ለኪሳራ ተዳርገዋል የተባሉ ፋብሪካዎች ወደ ስራ ባለመግባታቸው ምክንያት በተያዘው አመት በሃገር ውስጥ ከፍተኛ የስኳር እጥረት መፈጠሩን በሃገር ውስጥ ያሉ ጋዜጦች ዘግበዋል።

ለሃገር ውስጥ ገበያ ከሚያስፈልገው ወደ 543ሺ ቶን ስኳር ውስጥ 44 በመቶ አካባቢ ብቻ የሚሆነው የተመረት ሲሆን መንግስት 140ሺ ቶን ስኳርን በ71 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ከህንድ ማስገባት መጀመሩን ለመረዳት ተችሏል።

የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮሮፖሬሽን የስኳር ፋብሪካዎቹን ለመገንባት ሃላፊነት ቢሰጠውም መንግስታዊው ድርጅት ፋብሪካዎችን ወደ ስራ ማስገባት ሳይችል መቅረቱ መግለፁ ይታወሳል።

የህንድ መንግስትና ቻይና ለፋብሪካዎቹ ግንባታ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድርን አቅርበው የነበረ ሲሆን፣ መንግስት በበኩሉ ለፋብሪካዎቹ ግንባታ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ መመደቡ ታውቋል።

ይሁንና ስኳርን ከ3 አመት በፊት ለአለም አቀፍ ገበያ ያቀርባሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩት የበለስና እና የኩራዝ ቁጥር አንድ ፋብሪካዎች ግንባታቸው በ60 እና በ80 በመቶ ላይ መሆኑንን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

ግንባታቸው የተጀመረውንና ሌሎች በእቅድ ላይ ያሉ የስኳር ፋብሪካዎች ገንብቶ ለማጠናቀቅ መንግስት ወጪ ካደረገው ሶስት ቢሊዮን ዶላር በተጨማሪ 172 ቢሊዮን ብር በቀጣዩ አራት አመታት እንደሚያስፈልገው ብሉምበርግ በቅርቡ መዘገቡ ይታወሳል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው የውጭ ምንዛሪን ያስገኛሉ ተብለው የነበሩት ፋብሪካዎች ካጋጠማቸው ኪሳራ በተጨማሪ መንግስትን ለስኳር ግዢ መዳረጋቸው በኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫናን እንደሚያሳድሩ አስረድተዋል።

ፋብሪካዎቹ ያጋጠማቸውን ኪሳራ ተከትሎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስኳር ኮሮፖሬሽን ምንም አይነት የሰራተኛ ቅጥር እንዳያከናውን የደረሰም ኪሳራ በአግባቡ እንዲጠና ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።