መንግስት በወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ ተጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–ነሀሴ 22/2010) የፌደራል መንግስቱ በወልቃይት  ጠገዴ ጉዳይ  ጣልቃ እንዲገባ ተጠየቀ።

የፌደራል መንግስቱ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገባ የጠየቀው የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ነው።

ኮሚቴው  ባወጣው መግለጫ እንዳለው በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ ህወሓት እየፈፀመ ያለው በደል ወደ ባሰ አደጋ ሊሸጋገር ይችላል።

የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ እንደገለጸው የትግራይ መንግስት በወልቃይት፣ጠገዴና ጠለምት አካባቢ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን ከመንግስት ግምጃ ቤት መሳሪያ እያወጣ እያስታጠቃቸው ይገኛል።

በምዕራባዊ ዞን የወልቃይት፣ጠገዴና ቃፍታ ሁመራ አካባቢ ብቻ ሰባት የውትድርና ማሰልጠኛ ማዕከላትን በመክፈትም ለገበትሬዎች የውትድርና ስልጠና በመስጠት  ላይ ይገኛልም ብሏል ኮሚቴው።

እንደ ኮሚቴው ገለጻ የአካባቢው ሕዝብ በተወለደበት አካባቢ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥሮ ሀብቱ፣ንብረቱ እና መሬቱ ተቀምቶ ለትግራይ ተወላጆች ተሰጥቶበታል።

ማዕከላዊ መንግስቱም ይሕንኑ አውቆ እንዳላወቀ የሚያደርገው ዝምታ ነገ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል ነው ያለው።

በወልቃይት ጠገዴ  ዜጎች በግፍ ተገድለዋል  ዘመዶቻቸው ዕርማቸውን ሳይወጡ የሟች ዘመዶቻቸውንም መቃብር ሳያውቁ ይገኛሉ።

ሕዝቡ አማርኛ ቋንቋውንና አማራዊ ባህሉን እንዲያጠፋ የተለያየ ተፅዕኖ ይደርስበታልም ብሏል መግለጫው።

ይህ ሁሉ ወታደራዊ ዝግጅት ሲደረግም ማዕከላዊ መንግስቱ ዝምታን መምረጡ እግባብ አይደለም ነው ያለው።

ህብረተሰቡ እየተፈፀመበት ካለው ስነልቦናዊ ሽብርና ስጋት፣ አለፍ ሲልም ሰብአዊነት የጎደለው አካላዊ ጥቃትና መበደል ነፃ እንዲሆን መንግስት እጁን  እንዲያስገባም ኮሚቴው አሳስቧል።

ሕዝቡን በጉልበት መግዛት በፍፁም አይቻልም ያለው የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ መግለጫ የፌደራል መንግስቱ በአካባቢው የመከላከያ ሰራዊቱን በማሰማራት ሕወሃት በሕዝብ ላይ የሚፈፅመውን ግፍ ሊከላከል ይገባል ሲል አሳስቧል።