መንግስት በሃገሪቱ ለሚከሰቱ ግጭቶችና ችግሮች መፍትሄ መስጠት አለበት ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 21/2011) የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መንግስት በሃገሪቱ አንዳንድ ክፍሎች ለሚከሰቱ ግጭቶችና ችግሮች መፍትሄ መስጠት አለበት ሲል አሳሰበ።

ሲኖዶሱ ከጥቅት 11 እስከ 21/2011 ሲያካሄድ የነበረውን መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ አጠናቋል።

ሲኖዶሱ ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ በሰጠው መግለጫ እንደ ሃገር የሚታዩ  ችግሮች እየተባባሱ የሚሄዱ ከሆነ ችግሮቹ ከዚህም በላይ ሊባባሱ ይችላሉ ብሏል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ  ቤተክርስቲያኗ የበኩሏን ጥረት እንደምታደርግና የወንጌል ስምሪትን ከምንጊዜውም በበለጠ አጠናክራ እንደምትቀጥል ሲኖዶሱ በመግለጫው አስታውቋል።

በኢትዮጵያና ኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ  ቤተክርስቲያናት  እንዲሁም በምዕመናኖቻቸው መካከል የተሻለ መቀራረብ መፍጠር የሚያስችል ኮሚቴ መዋቀሩንም በመግለጫው ላይ ተቀምጧል።

ሲኖዶሱ በመግለጫው ከህዳር 1 እስከ ህዳር 7/2011 ዓመተ ምህረት ድረስ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ መመሪያ አስተላልፏል።

ሲኖዶሱ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት ያለችው ቤተክርስቲያን በአንዲት ቀኖናዊት ቤተክርስቲያን በማዕከል እንድትመራ መወሰኑንም በመግለጫው ላይ አስቀምጧል።

ጉባዔው በኢየሩሳሌም ዴር ሱልጣን ገዳም ላይ በግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እየቀረበ ያለው የባለቤትነት ጥያቄና ስራዎችን የማስተጓጎል ጥረት ሊቆም ይገባል ሲልም አሳስቧል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ የመሰነጣጠቅ ችግር ለደረሰበት የቅዱስ ላሊበላ  አብያተ ክርስቲያናት ጥገና የሚውል የ20 ሚሊየን ብር ድጋፍ  ማድረጉም ታውቋል።

ሲኖዶሱ የብፁዓን አባቶች የስራ ምደባና ዝውውር ማካሄዱም ታውቋል።