መንግስት ለኦነግ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

መንግስት ለኦነግ ማስጠንቀቂያ ሰጠ
( ኢሳት ዜና መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ/ም ) የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር ሊ/መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ፣ በመንግስት እና በድርጅታቸው መካከል ትጥቅ የመፍታት ስምምነት እንዳልተካሄደ የሰጡት መግለጫ፣ መንግስት በኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር ዲኤታ በአቶ ካሳሁን ጎፌ በኩል መግለጫ እንዲሰጥ ተገዷል።
አቶ ካሳሁን እንዳሉት ኦነግ ሰላማዊ ትግሉን ሲቀበል ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ የሚታወቅ እንጅ ለብቻው ተነጥሎ ድርድር የተካሄደበት አለመሆኑን ገልጸዋል።
ኦነግ በትግራይ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ትጥቁን ፈትቶ መግባቱንና ታጣቂዎቹም በአሁኑ ሰዓት ስልጠና ላይ መሆናቸውን የገለጹት ባለስልጣኑ፣ የኦነግ አመራር የሚሰጠው እርስ በርስ የሚጋጭ መግለጫ በፍጥነት ሊስተካከልና ኦነግም ትጥቅ ያልፈቱ አባሎቹን ትጥቅ እንዲያስፈታ ጠይቀዋል። ይህ ካልሆነ ግን መንግስት ትጥቅ የማስፈታቱን ስራ ራሱ እንደሚያከናውን ገልጸዋል።
በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በወለጋ እና በተለያዩ የሞያሌና ጉጂ አካባቢዎች የመንግስት ተቋማትን ተቆጣጥረው የተለያዩ ውሳኔዎችን እየወሰኑ ነው። በቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ በቅርቡ ለተፈጠረው በመቶ ሺ ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል እና ቁጥሩ በውል ላልተወቀ ዜጎች ሞት ምክንያት የሆነው ግጭት በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መጀመሩን የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት ገልጸው ነበር።
በጉጂ፣ ቦረና እና ወለጋ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችም የኦነግ ታጣቂዎች እየወሰዱት ባለው እርምጃ ስጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
አቶ ዳውድ ኢብሳ ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ድርጅታቸው በሰላማዊ መንግድ ለመታገል ወደ አገር ውስጥ መግባቱንና በምርጫውም እንደሚሳተፍ አስታውቀዋል። ይሁን እንጅ በተለያዩ አካባቢዎች በድርጅታቸው ስም ስለሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የሰጡት ግልጽ ማብራሪያ የለም።
በሌላ በኩል ደግሞ በድርጅቱ ኦነግ ከተቀረው “የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አብሮ መኖር ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ህዝበ ውሳኔ እንዲሰጥ መደረግ እንዳለበት የያዘውን አቋም አለመቀየሩን አቶ ዳውድ አስታውቀዋል። ይህን አላማውን በምን መንገድ እንደሚፈጽመው ግን አቶ ዳውድ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም።