መንግስት ለሜቴክ የተሰጠውን የማዳበሪያ ፋብሪካ በመቀማት ለአለማቀፍ ጫረታ ሊያቀርብ መሆኑ ተጠቆመ

መንግስት ለሜቴክ የተሰጠውን የማዳበሪያ ፋብሪካ በመቀማት ለአለማቀፍ ጫረታ ሊያቀርብ መሆኑ ተጠቆመ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 23 ቀን 2010 ዓ/ም) ብሉምበር የመንግስት ባለስልጣናትን በመጥቀስ እንደዘገበው እርምጃው አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ለመከላከያ ሰራዊት በአድሎ የሚሰጡትን ፕሮጀክቶች ለማምከን የገቡትን ቃል ወደ ተግባር እየለወጡት መሆኑን ማሳያ ነው። የያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካን ለመገንባት መንግስት በህወሃት ጄኔራሎች ለሚመራው የመከላከያ እና ምህንድስና ተቋም ስራውን ቢሰጥም ፣ ተቋሙ ግን በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከማባከን ውጭ ይህ ነው የሚባል ስራ ሳይሰራ ቆይቷል። የመንግስት ድርጅቶች የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ እንደገለጹት፣ የኮንትራት ስምምነቱ እንደሚቋረጥና ስራው ለሌላ ኩባንያ እንደሚሰጥ ስምምነት ያለ ቢሆንም፣ የመጨረሻ ውሳኔ ግን አልተሰጠበትም። በአዲሱ ጨረታ የአለማቀፍ ኩባንያዎች ጭምር ሊሳተፉበት እንደሚችሉ ባለስልጣኑ ገልጸዋል።
ሜቴክ የያያ የማዳበሪያ ፋብሪካን በሁለት አመት ስርቶ ለመጨረስ የዛሬ 6 አመት ከመንግስት ጋር የ 11 ቢሊዮን ብር ስምምነት ፈርሞ ነበር። ከ6 አመት በሁዋላ ደግሞ ስራው በግማሽ እንኳን ሳይጠናቀቅ ተጨማሪ 20 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ጥያቄ አቅርቦ ነበር።
ሜቴክን ለረጅም አመታት የመሩት የህወሃቱ ጄ/ል ክንፈ ዳኘው በዝርፊያና በአስተዳደር መበላሸት ድርጅቱ ላወደመው ከ100 እስከ 200 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሃብት ተጠያቂ ሳይሆኑ ዶ/ር አብይ ጠ/ሚኒስትር ሆነው እንደተመረጡ ስልጣናቸውን ለቀዋል። በእርሳቸው ቦታ የተተኩት የቀድሞው የንግድ ሚኒስትር አቶ በቀለ ቡላዶ ኩባንያው በአለማቀፍ ኦዲተሮች እንዲመረመር በማድረግ ጄ/ል ክንፈንና በዙሪያቸው ያሉ የህወሃት ወታደራዊ አዛዦችንና ባለስልጣናትን ለፍርድ ያቅርቡ አያቅርቡ የታወቀ ነገር የለም።