ሕወሃት የንጹሃንን ደም ከማፍሰስ እንዲቆጠብ ተጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 2/2010)

በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የንጹሃንን ደም ከማፍሰስ ድርጊቱ እንዲቆጠብ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አንድነት እንዳይመጣ መሰናክል ከመሆን እንዲታቀብ ብጹእ አቡነ ኤዎስጣጤዎስ ጥሪ አቀረቡ።

የመከላከያ ሰራዊት አባላትም ተግባራቸው የውጭ ወራሪን መመከት እንጂ ወገንን መግደል እንዳልሆነም መገንዘብ ይኖርባቸዋል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የካሊፎርኒያ ሊቀጳጳስ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በዋሽንግተን ሲያትል ከተማ የሚያገለግሉት ብጹእ ዶክተር አቡነ ኤዎስጣጤዎስ የሰው ልጅን የሚያህል “ሕንጻ እግዚአብሔር እየፈረሰ ልማቱ ለማን ነው? በማለትም ጠይቀዋል።

የወልዲያውን ጭፍጨፋ ላወገዙትና የተከሰተውን ሁኔታ ለአለም ለመሰከሩት ለሰሜን ወሎ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ለብጹእ አቡነ ኤርሚያስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

“ሰዎች የትኛውንም እምነት ይከተሉ፣የትኛውንም ቋንቋ ይናገሩ የእግዚአብሔር ሕንጻዎች ናቸውና አናታቸውን እየመቱ መግደል የእግዚአብሔርን ሕንጻ እንደማፍረስ ይቆጠራል።ደማቸውም ቢሆን ፈሶ አይቀርም፣እግዚአብሔር ምላሹን ይሰጣል።”ሲሉ ሃዘንና ቁጭታቸውን ይገልጻሉ።

ብጹእ ዶክተር አቡነ ኤዎስጣጤዎስ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት በ1997 የአጣሪ ኮሚሽን አባል በነበሩበትም ወቅት የታዘቡትን ሲናገሩ ብዙዎቹ የሞቱት ግንባራቸው ላይ በጥይት ተመተው ነው።

ይሔም ሆን ተብሎ የተፈጸመ ለመሆኑም በአጣሪ ኮሚሽን አባልነታቸው የሰጡትንም ምስክርነት አስታውሰዋል።

ዛሬም በእሬቻ በአል ላይ በቢሾፍቱ፣በአምቦ፣በጎንደርና በባህርዳር እንዲሁም በወልዲያ የፈሰሰው ደም ወደ እግዚአብሔር ጮኾ ይጣራል ብለዋል አቡነ ኤዎስጣጤዎስ።

“ነፍሰ ገዳዮች ምንግዜም ቢሆን ሰላም የላቸውም ቃዬልን ተመልከቱ” ሲሉ መጽሀፍ ቅዱስን መሰረት አድርገው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ብጹእ አቡነ ኤዎስጣጤዎስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረውም ችግር እንደሚፈታ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

አባቶቹን ወደ አንድነት ለማምጣት መንግስት እንቅፋት ሆኖ መገኘቱን እንደሰሙ ገልጸዋል።

ለርሱም ቢሆን በዚህ በመጨረሻው ሰአት የቤተክርስቲያኒቱን አባቶች አንድ እንዲሆኑ ቢያደርግ ይበጀዋል ሲሉም ይመክራሉ።

ከአጣሪ ኮሚሽን አባልነታቸው ጋር ተያይዞ እውነቱን በመመስከራቸው ሟቹ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና ሟቹ የቀድሞው ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ በቡድንና በግል ጠርተው የተናግሯቸውን፣ ያስፈራሯቸውንና የገሰጿቸውን ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በዝርዝር ዳሰዋል።

በዚህም ሳቢያ እስከ በስደት ላይ ሆነውም የተከተላቸውን ፈተና በዝርዝር ተመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ዋሽንግተን ግዛት ሲያትል ከተማ የሚገኘው የደብረ ገሊላ ቅዱስ ባለወልድ ቤተክርስቲያን የበላይ ሃላፊ ከሆኑት ከብጹእ ዶክተር ኤዎስጣጤዎስ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ የፊታችን ረቡዕ የካቲት 7/2010 ይዘን እንቀርባለን።