ሒዩማን ራይት ዎች የለውጥ ሒደት ላይ እንቅፋት እየተፈጠረ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 10/2010)በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች በተጀመረው የለውጥ ሒደት ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ መሆኑን ሒዩማን ራይት ዎች ገለጸ።

ሒዩማን ራይትስ ዎች እንዳለው በኢትዮጵያ በብሔርና በሃይማኖት ሰበብ የሚካሄዱ ግድያዎች ከፍተኛ ውጥረት በመፍጠር ላይ ናቸው።

በተለይም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች በለውጡ ሂደት ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ ነው ብሏል ሒዩማን ራይትስ ዎች።

ይህ በእንዲህ እንዳለም መንግስት ለውጡን የሚያደናቅፉ ግጭቶችን እንዲያስቆም የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የተሰኘው ተፎካካሪ ፓርቲ ጠይቋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ የማሻሻያ ርምጃዎች መካሄዳቸውን ተከትሎ በሃገሪቱ ትልቅ ተስፋ መፈንጠቁን ሒዩማን ራይትስ ዎች ገልጿል።

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በወሰዱት ርምጃ በሃገሪቱ ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳስገኘላቸውም የሰብአዊ መብት ተከራካሪው ድርጅት አስታውሷል።

ይህም ሆኖ ግን በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ለውጡን እንዳያደናቅፉ ስጋት መኖሩን ሒዩማን ራይትስ ዎች ገልጿል።

እናም ተቋሙ መንግስት በተለይም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የሚፈጸሙ ግድያዎችን ካላስቆመ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የለውጥ ተስፋ ሊደናቀፍ ይችላል ብሏል።

ሒዩማን ራይትስ ዎች እንደገለጸው በኢትዮጵያ በብሔርና በሃይማኖት ሰበብ የሚካሄዱ ግድያዎች ከፍተኛ ውጥረት እየፈጠሩ ናቸው።

በተለይም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ያሉ ግጭቶች ለበርካታ ሰዎች መገደል ምክንያት ናቸው ሲል ገልጿል።

በቅርቡ ብቻ በኦሮሚያ ምስራቅ ሐረርጌ 41 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

በሶማሌ ክልል ደግሞ ከ96 በላይ ሰዎች ተገድለው ከ10 የማያንሱ አብያተክርስቲያናት መቃጠላቸው የችግሩን አሳሳቢነት ያመለክታል።

በደቡብ ክልል ሸካ ዞንም በቴፒ ብሔርን መሰረት ባደረገ ግጭት ከ4 በላይ ሰዎች መሞታቸው አይዘነጋም።

ይህ በእንዲህ እንዳለም መንግስት ለውጡን የሚያደናቅፉ ግጭቶችን እንዲያስቆም የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ጠይቋል።

የፓርቲው አመራር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በጉዳዩ አሳሳቢነት ዙሪያ በመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ለውጡን ለማደናቀፍ የታለሙ በመሆናቸው በብዙዎች ዘንድ እየተወገዙ ያሉ ተግባራት ሆነዋል።